“ሰነፍ እረኛ ከቅርብ መልስ ሲሉት እንቢ ብሎ ሲሮጥ ይውላል!”

‹‹ሰነፍ እረኛ ከቅርብ ሲሉት እምቢ ብሎ ሲሮጥ ይውላል››
………………………………………………………………..
ሞገድ እጅጉ
‹‹ሰነፍ እረኛ ከቅርብ ሲሉት እምቢ ብሎ ሲሮጥ ይውላል›› የሚባል አባባል አለ፡፡ የአባባሉ ትርጉም ከብት ለሚጠብቁ እረኞች ነው፡፡ እረኞች ከብት ሲጠብቁ፤ ከብቶች ወደ እህል እንዳይሄዱ፣ ወደ ገደል እንዳይሄዱ፣ በአጠቃላይ ጉዳት እንዳያደርሱ፣ በራሳቸውም ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በእረኞች ይጠበቃሉ፡፡
ታዲያ ሰነፍ እረኛ ከብቶች መሄድ ወደማይገባቸው ቦታ መሄድ ሲጀምሩ ‹‹መልሳቸው›› ሲባል ሰነፍ ስለሆነ ችላ ይላል፡፡ አሁንም ትንሽ ራቅ ሲሉ ‹‹ኧረ መልሳቸው›› ሲባል ሰነፍ ነውና ዝም ይላል፡፡ በመጨረሻም ከብቶቹ ከዓይን ይጠፋሉ፡፡ ከዓይን ጠፉ ማለት ከሰው እህል ይገባሉ ወይም የሚተናኮላቸው አውሬ ያጋጥማቸዋል ማለት ነው፡፡ ይህኔ እረኛው መሮጥ ይጀምራል፡፡ ገና ከዓይኑ ሳይጠፉ፣ ገና ከቅርብ እያሉ ቢመልሳቸው ግን ይህን ያን ያህል አይሮጥም ነበር፡፡ ወይም ከብቶች ከሰው እህል ገብቶ አይገረፍም ነበር፤ ወይም ከብቶች ገደል ገብተው የንብረት ጉዳት አይደርስም ነበር፡፡ ‹‹ሰነፍ እረኛ ከቅርብ መልስ ሲሉት እምቢ ብሎ ሲሮጥ ይውላል›› የሚባለው ለዚህ ነው፡፡
ይህ አባባል የአማራን እና የአዲስ አበቤን ስህተት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ በተለይ አዲስ አበቤ ልክ እንደ ሰነፉ እረኛ ሆኗል፡፡ ከቅርብ መልስ ሲባል እምቢ ብሎ እነሆ ዛሬ መመለስ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ እነሆ ዛሬ ከባለቤትነት ወጥቶ መጤ ሆኗል፡፡ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንዳልነው ከዓመታት በኋላ መጤ ተብሎ ይባረራል፡፡
መስቀል አደባባይን በማደስ ስም ሲነጥቁት ‹‹ልማት ምን ችግር አለው?›› ሲል ነበር፡፡ እስክንድር ነጋ ነገርየው ለልማት አይደለም፤ ታሪክ ማጥፋት ነው ብሎ ሲታገል ‹‹እስክንድር አበደ፤ አማኑኤል ይወሰድ›› ሲል ነበር፡፡ ዛሬ መስቀል አደባባይን አጥቷል፡፡
ዓድዋ ዜሮ ዜሮ ፕሮጀክት ሲጀመር ‹‹ጉዳዩ ታሪክ የማጥፋት ነው›› ሲል አሁንም ‹‹እስክንድር አበደ›› ሲባል ነበር፡፡ እነሆ ዛሬ የዓድዋ ዜሮ ዜሮን ውበት ታበላሻለህ ተብሎ ከፒያሳ ተጠራርጎ ጠፍቷል፡፡ ዛሬ ፒያሳ ላይ አንድ ነዋሪ የለም፡፡ ያሉት ጥቂት ንግድ ቤቶችም በሚቀጥሉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ውስጥ ይነሳሉ፡፡
እነሆ በቅርቡ ደግሞ ‹‹የኮሪደር ልማት›› በሚል ሙሉ አራት ኪሎና አዲስ አበባን ሲያፈርሱ፣ ከአራት ኪሎ እስከ መገናኛ ያሉ ቤቶችን ሲያወድሙ፣ ከመገናኛ እስከ አያት ድረስ ያሉ ቤቶችን ሲያፈርሱ ‹‹ከተማዋ ብታምር ምን ችግር አለው?›› ሲሉ ነበር፡፡ ብታምር፣ ብትጸዳ፣ ብትበለጽግ ምንም ችግር አልነበረውም፡፡ ችግሩ ግን ከተማዋን የማዘመን ሥራ ስላልሆነ ነው፡፡ ጉዳይ ‹‹መጤ›› የሚሉትን ሕዝብ የማፈናቀልና የማጥፋት ሥራ መሆኑን እነሆ ከ6 ዓመታት ጥፋት በኋላ እንኳን አልገባውም፡፡
እዚህ ላይ አንድ ማረጋገጫ ልብ እንበል፡፡ ‹‹የኮሪደር ልማት›› ከሚባለው የጥፋት ፕሮጀክት ውስጥ በጥራት አንደኛ የተባለው የአራት ኪሎው ነው፡፡ የሚያሳዝነው ነገር እነሆ ተመረቀ በተባለ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የእግረኛ መንገዱ ወላልቋል፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ በሰርጓች መርከብ የተመታ ይመስል እግረኞች እየዘለሉ የሚሻገሩት ሆኗል፡፡ በቅርቡ በማህበራዊ ገጾች ሲዘዋወር በነበረው ፎቶና ቪዲዮ እንደታየው ዝናብ ሲዘንብ አስፋልቱ አላሻግር ብሎ ሰዎች እየተዟዟሩ ሲጉላሉ ነበር፡፡ ከምንም በላይ ግን ትልቁ ችግር የተሰራው የእግረኛ መንገድ መነቃቀል ጀምሯል፡፡ በአንድ ወር ውስጥ መፍረስ የጀመረ ሥራ ከሦስትና አራት ዓመታት በኋላ የእርሻ ማሳ ይመስላል ማለት ነው፡፡ ይሄንን ነው እንግዲህ ‹‹ጥሩ ሲሰራ እናመስግን›› የተባለው፡፡
‹‹የኮሪደር ልማት›› የተባለው የጥፋት ፕሮጀክት ዋና ዓላማው ነባር የነበረውን ምንነት ማጥፋት ነው፡፡ ለዚህም ነው ከአራት ኪሎ እስከ መገናኛ ድረስ እየተሰራ ያለውን የእግረኛ መንገድና የአስፋልት ዳርቻ የኦሮሞ መለያ ነው ብለው በሚያስቡት የዋርካ ዛፍ ምስል የሰሩት፡፡ ሁሉም የእግረኛ መንገዶች ዳርቻ የኦዳ አርማ ተደርጎባቸዋል፡፡ አዳነች ‹‹አዲስ አበባ የሁላችንም ናት›› እያለች እያጃጃለች የአንድ ብሔር መለያ ነው የተበለውን የዛፍ ምልክት የከተማዋ መለያ አድርጋዋለች፡፡
አራት ኪሎ የሚገኘው የአራዳ ክፍለ ከተማ ግቢ ሙሉ በሙሉ የኦሮሞ ባንዲራ ነው በሚባለው የግብጽ ምልክት በሆነው ነጭ፣ ቀይና ጥቁር ቀለም አሸብርቋል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው አዲስ አበባ ሙሉ በሙሉ የኦሮሞ ብቻ ናት በሚል ነው፡፡ ሌላው መጤ ነው በሚል ነው፡፡
‹‹ሰነፍ እረኛ ከቅርብ ሲሉት እምቢ ብሎ ሲሮጥ ይውላል›› ከራቀው በኋላ እንኳን መሮጥ አልጀመረም!

Discover more from wenchifEthiopia.com ወንጭፍ ኢትዮጵያ

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading