አዲስ አበባን እና አዲስ አበቤን ጠልነት በታሪክ መነፅር፣ ከጥንት እስከ ዛሬ…

ወይ አዲስ አበባ…!

ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ
ሀገርም እንደ ሰው ይናፍቃል ወይ?

ክፍል.1

“ሀገር ማለት ሠው ነው፣ ሠውም ማለት ሀገር”…  የሚለው የልሂቃን ፖለቲካዊ ፍልስፍና፣ የጠቢብ ሰዎች የብዕር ክትበት አሻራ ብያኔ፣ በአንድ የአስናቀች ወርቁ ዘፈን ግጥም ውስጥ፣ “እጥር ቅንብብ” ብሎ በአይረሴ ዜማ ቅኝት ውስጥ ተገኝቷል።
አይ ጥበብ፣ ጥበብማ ነበረን…!

ስለ ዜማ እና ሙዚቃ ግጥም ላወራላችሁ አይደለም። ተወልጄ  ስላደኩበት ሀገረ ምድሬ፣ ስለ “አዱ ገነት” አዲስ አበባ እና “ሰው” እንጅ… 

አዲስ አበባ፣ የድል እና አሸናፊነት ምሳሌ፣ የኢትዮጵያውያን ክብረ ማንነት መገለጫ፣ የአንድነት እና ህብረት መታያ ከተማነቷን በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ፀሀፍቶች መስክረውላታል። ግጥም ተገጥግጦላታል፣ ሙዚቃ ተሞዝቆ፣ ባለቅኔ ተቀኝቶላታል።

አዲስ አበባ፦ የጥቁር ህዝቦች ታላቅ ድል #አድዋ ክተት የተነገረባት፣ መክረው ዘክረው በቃል ኪዳን መኃላ ተሳስረው የተነሱባት፣ ከድል መልስም የአሸናፊ ንጉሱ እምዬ ሚኒሊክ የጦር አበጋዞች ኮረብታዎቿን ከብበው ከትመው የተቀመጡባት፣ የደጃቾች፣ የራስ እና ሊቀመኳሶች ምድረ እርስት፣ የነገስታቱ ዙፋን ፅኑ መሰረት፣ የአፍሪካውያን ኩራት ምንጭ አሻራ መታያ መድረክ ሆና የተቆረቆረች እፁብ ድንቅ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ ያላት፣ ለአዳም ልጆች ተመች ዘንድ ተፈጥሮ  ያደላት፣ ለወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እስትራቴጅክ ከተማ ነች፣ ሸገር አዲስ አበባ።

የአዲስ አበባ ልጅ ነኝ፣ ያውም የጃን ሜዳ…
ከልዑላኑ ጋር ፈረስ የሰገርኩኝ፣ ጠዋትና ማለዳ…

የማን ግጥም እንደሆነ ባላውቅም፣
ግጥሟ በጭንቅላቴ ታትማ እንድትቀር የሆነችው ሰፈሬ፣ ተወልጄ ያደኩባት ጃንሜዳን ስለምታሞግስልኝ ክብረ መገኛየ “ጃንዬን”  ከፍ ያለ ማማ ላይ አውጥታ ስላሳየችልኝ ይመስለኛል።

ምን፣ ልል እየፈለግሁ ይሆን? ጉዳዬ ወዲህ ነው።

ተወልጄ ያደኩባት፣ የጎረመስኩባት ክብረ መገኛዬ አዱ ገነት “አዲስ አበባ” የከተማዬን ታሪካዊ ዳራ እና አውዳዊ የገጠማትን ህልውናዊ ፈተና ከጥንተ ታሪኳ ጋር አጋምጄ ለማሳየት የሞከርኩት እንዲሁ ለዘበት አይደለም። ከተማዬ፣ ኩራቴ፣ ትውልድ መንደሬ፣ ትዝታዬ የሆነችው አዲስ አበባ የዛሬው ችግሯ፣ ሳንካና ውጣውረድ ፈተናዋ ስረ መሰረት አመክንዮ ለመረዳት፣ የዘመን ጅረት መነሻን ፈልጎ መድረስ፣ ወደ መፍትሄው ፍለጋ ግማሽ መንገድ ስለሚገፋን ነው።

አዲስ አበባ በጣልያን ዳግም ወረራ
======================

ፋሽስት ጣልያን የአድዋን ድል፣ የ 40 ዓመት በቀል ለመፈፀም እና አዲሱ የቅኝ ግዛት ተስፋፊነት እቅዷ ስኬት   በትውልድ ቅብብል አሰላስላ፣ ትጥቅ እና ስንቋን አደራጅታ በድጋሚ ስትወርረን፣ እንደቀደመው አንድ ሆነን ድል በማድረግ ፋንታ በውስጥ መሳፍንታዊ ሽኩቻ ተዳክመን በመገኘታችን፣ ማይጨው ላይ በእርስ በእርስ ሽኩቻ አሻጥር በራስ ወገን ከጀርባ ተወግተ ተሸነፍን። ጣልያንም የሰሜን ተራሮችን አልፋ የነገስታቱ መቀመጫ፣ የነፃነት መታሰቢያ የድል ምልክት አሻራዎች ደምቀው ወደሚታዩባት… የአድዋ ድል ባለ ግርማዎች
አፄ ሚኒሊክ
እቴጌ ጣይቱ
ራስ መኮነን
እና ብዙ ባላምባራሶች አፅመ እርስት መገኛ፣ በግርማ በመታሰቢያቸው ደምቀው መድረኳ ወዳደረጓት አዲስ አበባ ገሰገሱ፣ ደረሱም።

ይህ ማስረጃን በሀበሻ ጀብዱ ተጫነ ጆብሬ በተረጎመው የችኮዝላቫኪያዊ ዜጋ መፅሀፍ
በቀ.ኃ.ስ ግለ ታሪክ መፅሐፍ ላይ ታሪከ ሀተታው አለ።

በአሻጥር ከተሞላው እና ሚዛናዊ ሰልፍ ባልነበረው የማይጨው አውደ ውጊያ በመሸነፋችን፣ ይች፣ ታላቅ የአሸናፊነት መንፈሰ ድባብ የሰፈፈባት፣ የነገስታቱ ታሪከ ዓምድ ገዝፎ የሚታይባት፣ የአራድነት መድረኳ፣ የንቃት ማዕከለ ፈርጥ ሸዋ ምድር በወርሃ ግንቦት 1929 ዓ.ም  በጠላት ፋሽስት ጣልያ መዳፍ ላይ ወደቀች።

የአዲስ አበባ እና አዲስ አበቤ ህልውና አደጋ አሀዱ አለ!========================

የጥንታዊቷ የዳዊት ከተማ “በረራ” መታሰቢያ እንድትሆን በዳግማዊ ሚኒሊክና እቴጌ ጣይቱ ብጡል በ1887 ዓ.ም በዳግማዊ ሚኒሊክ ፈቃድ በባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ የተቆረቆረችው ዘመናይቷ የሸዋ ጠቅላይ ግዛት እና የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የንጉሰ ነገስቱ ቤተ መንግስት ያረፈባት የልዑላን እና መሳፍንቱ፣ የነፍጠኞች ጦር ማዘዣና መቀመጫ መዲና አዲስ አበባ እና ህዝቧ የህልውና አደጋ በጣልያን እጅ ከወደቀችበት ከዚህ ዘመን 1929 ዓ.ም ይጀምራል።

አዲስ አበባ እና አዲስ አበቤ በፋሽስት ጣልያን መዳፍ
===================
=====
ሞሶሎኒ፣ በሮም አደባባይ ህዝቡን ሰብስቦ በጉራ እየተውረገረገ አዲ አበባ በእጁ መግባቷን ሲያበስር፣ ከተማዋ በእልልታ ጮቤ ረገጠች፣ ቀለበታቸውን ከእጣታቸው እያወለቁ በመስጠት ኢትዮጵያ መወረሯን የደገፉ የጣልያን እንስቶች በደስታ ፈጠዝያ አልተቻሉም፣  መድፍ እና ታንክ ባርካ ፋሽስት ጦሩን የሸኘችው የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የደስታ ደወል አስደወለች። ፖፕ ወጥቶ ለህዝቡ “እንኳን ደስ ያላችሁ፣ አዲስ አበባ በእጃችን ገባች” አለ።

ነገር ግን፣ ምድረ ሀበሻ፣ በዚያች ቀን ፀጥ ረጭ ብሎ ዋለ።

ወርሃ የካቲት የቅዱስ ሚካኤል እለት 1929 ዓ.ም የአዲስ አበባ ወጣቶች ፋኖነት መንፈስ በልባቸው  ተቀጣጠለ። ሞገስ አስግዶም እና አብርም ደቦጭ፣ ከተማዋን ተቆጣጥሮ ይፈነጭ፣ ይሞሸር፣ ይደግስ፣ ይደነፋ የነበረው ቧራቂ የፋሽስት ወታደሮች ዋና አዛዥ ግራዢያኒ  ላይ የቦንብ ጥቃት አደረሱ።

ግራዚያኒ እና ጠባቂዎቹ ክፉኛ ቢቆስሉም አልሞቱም። ነገር ግን፣ የግራዚያኒ የበቀል እርምጃ የከፋ ሆነ።
አዲስ አበባ የፋሽስቶች ክፉ ዘር ፍጅት ሰለባ ሆነች።  ጣልያኖች አስቀድመው ለወረራ ሢነሱ በልዩ ትኩረት በኢላማነት ሊስት ያደረጓቸውን
•ኦርቶዶክሣውያንን
•አማራዎችን
•የነገስታት ቤተሰቦች
•የተማሩትን እየመነጠረች ጨፈጨፈች። ቤት እየዘጋች አቃጠለች። የከተማው ነዋሪ 75% አማራዎች፣ ካህናት እና የተማሩት በአብዛኛው ተጨፈጨፈ። የአዲስ አበባ ጎዳናዎች በደም ጎርፍ ተሸፈኑ። ከተማዋን የቆረቆሩት የነፍጠኛ ጀግና ቤተሰቦች፣ ልጆች፣ ሚስቶች አስከሬን በየጎዳናው ክምር ሰራ። ቤቶች በእሳት ተንቀለቀሉ። የተረፈው እግሩ በመራው ተሰደደ። በየጫካው ለጅብ ሲሳይ ሆነው የቀሩት እልፍ ናቸው።
ከ35 ዓ.ም በፊት የደረሰባቸውን ሽንፈት እና ለሽንፈታቸው ዋና ምክንያት ያሉትን  ማህበረሰብ እና ቤተ እምነት ትኩረት አድርገው አጠቁ።
በደም በተነከረ እጃቸው ወደ አዲስ አበባ አራቱም አቅጣጫ እየካለቡ ተዘዋወሩ። ጠላት ሲሉ የፈረጁትን ህዝብ እና መሪያቸው ሚኒሊክ መታሰቢያን ከከተማዋ መታሰቢያቱን እናጠፋለን አሉ።

የጣልያን ግብረ ስራ አዲስ አበባን በተቆጣጠረ ማግስት
ጣልያን አዲስ አበባን እንደተቆጣጠረ የመጀመሪያ ያደረጋቸው ግብረ ስራዎች ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ነበሩ።
1ኛ. በአድዋ ድል፣ መታሰቢያነት የተሰሩ ማናቸውም ቅርሶች እና ግንባታዎችን ማፍረስ
2ኛ.  ጦርነቱን የመሩ እና እቅድ ያወጡ አመራሮች መታሠቢያ ስም እና ሀውልቶች መቅበር

3ኛ. አዳዲስ ግጭት ፈጣሪ ትርክቶችን ፈጥረው የጎሳ ግጭቶችን ለመቀስቀስ መንቀሳቀስ፣ ምሳሌ ኦሮሞው በአማራ ላይ እንዲነሳ የዘር ፍጅት እንዲፈፅም ማድረግ
4ኛ. የአዲስ አበባ ቆርቋሪ አማራ ህዝብን ከከተማው እንዲጠፋ  ማሳደድ እና የዘር ፍጅት መፈፀም። (1929ዓ.ም የካቲት 12) የተፈፀመው የአዲ አበባ ጭፍጨፋን ተመሥገን ገብሬ እና አልቤርቶ ሶባኪ የተባለው ጣልያናዊ ተሳታፊ በየመፅሃፋቸው ይሄን ማንነት ተኮር የአዲስ አበባን ጭፍጨፋ  እማኝ ሆነው መስክረዋል

ጣልያንአዲስ አበባ እና አዲስ አበቤን የአድዋ ሽንፈቴ ምክንያት የሆኑት ንጉስና ራሶች ቤተሰብ መገኛ በመሆኗ እንደነገስታቱ እና የጦር አበጋዝ ልጆች መገኛ በመሆኗ መበቀል አለብን፣ ህዝቡንም ልንራራለት አይገባም በሚል የፈፀሙት የጭካኔ እርምጃ ነበር።

እንዳሰቡትም፣ ጣልያን አዲስ አበባ እና ደቡቡን ኢትዮጵያ ክፍል በሙሉ  ከተቆጣጠረ በኋላ ፀረ አማራ አቋም በማራመድ፣ በመላው ደቡባዊ እና ምስራቅ ኢትዮጵያ አማርኛ ሲናገር የተገኘ በተገኘበት እንዲገደል፣ ቋንቋው በቢሮክራሲም አገልግሎት እንዳይሰጥ አስደርጋለች።
የጀነራል ጃጋማ ኬሎ(የበጋው መብረቅ) ፍቅረ ማርቆስ ደስታ የከተበው ግለ-ለታሪክ መፅሐፍ የዚያንን ዘመን ሀቀ ተጋድሎ ያትታል።

ከሁሉም፣ በሚልቅ፣ አዲስ አበባ እና ነዋሪዋ የወራሪዋ ጣልያን የ5 ዓመት ቆይታ የመከራ ቀንበር የከበደባት መዲና ነበረች። ምክንያታቸው ደግሞ፣ የአድዋ ድልን የመሩት ነገስታቱ፣ ራሶች እና ቤሰቦች፣ የልጅ ልጆች መገኛ ናትና ከተማዋ መውደም፣ ነዋሪዎቿ  መደምሰስ፣ መታሰቢያ ቅርሶችም መፈራረስ አለባቸው ብለው በማመናቸው ነበር። በዚህ ምክንያት በዳግማዊ ሚኒሊክ ሴት ልጅ ዘውዲቱ የተሰራው አራዳ ጊዮርጊስ የሚገኘው የሚኒሊክ ኃውልት እና ለገሃር የሚገኘው የሞዐ አንበሳ መታሰቢያ ኃውልትን ነቅለው በማንሳት ወደተሰወረ ስፍራ ወስደው በመሬት ስር ቀብረዋቸዋል።
የነገስታቱ እና አርበኞች መታሰቢያን፣ ቅርስ የሆኑ መኖሪያ ቤታቸውንም እየደረመሱ ለእነርሱ ምቹ ያሏቸውን አዳዲስ ከተማዎች በመቀየስ ታሪክ እና ዝክረ ገድል መታሰቢያ እንዳይኖራቸው ለማድረግ ጥረት አደረጉ። ይልቁንስ የፋሽስቶቹ መታሰቢያ የሚሆኑ አሻራቸው የሚገለጥባቸው ጣልያንኛ ስም የያዙ ሰፈሮችን እንደ አዲስ ቆረቆሩ። ለምሳሌ፣ መርካቶ እና ፒያሳ ይሄንን ገላጭ ምስክር ሆነው ዛሬም ድረስ አሉ።

በአዲስ አበባ የወራሪው ፋሽስቱ ጣልያንን አሻራ ለመትከል ሲባል ብቻ… በአድዋ ጀብደኞች ልጆች በሚል ፍረጃ በግፍ የከተማዋ ከ70% በላይ ህዝቧ ተጨፍጭፎ ተገድሎባታል። ንብረቱ እየተዘረፈ ተሳዷል። ከተማዋ፣ ለቆርቋሪዎቿ ባዳ እና አቅበዝባዥ እንድትሆን አድርገው የታሪክ ጠባሳ ጥለውልን አልፈዋል።

የጣልያን ፀረ-አማራ መርዛማ ትርክት ሰለባው የተማሪዎች ንቅናቄ እና አዲስ አበባ

1953 ዓ.ም ለከሸፈው መፈንቅለ መንግስት የትርክት እርሾ አቀባዩ የነዋለልኝ እና ጥላሁን ግዛው የተመራው የተማሪዎች ንቅናቄ ይፋዊ ስሁት የትርክት አቋም ነበር።

1953 ዓ.ም ላይ ከተሞከረችው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ክሽፈት በኋላ ለጥቃ ቀስበቀስ ውስጥ ለውስጥ የመቀጣጠል ድንገት ቦግ ብሎ የተከሰተው የ1966 ቱ አቢዮት የጣልያን ፀረ-አምሓራ እና ፀረ-ኦርቶዶክስ ትርክት በሶሻሊዝም ታጅሎ የተተገበረበት፣ ከጣልያን ጭፍጨፋ የተረፉትን የነገስታቱን መሰረተ ልሂቃን፣ እንዲሁም ንቁ ተማሪዎችን በፊውዳል፣ ቡርዣ እና ፀረ-አቢዮተኛነት በመፈረጅ አብዛኛዎቹን የአምሓራ ልሂቃን ከአዲስ አበባ እና መላዋ ኢትዮጵያ እየረሸነ የፈጀበት ጥቁር ዘመን አለፈ።

መላኩ ተፈራ የእግዜር ታናሽ ወንድም
የዛሬን ማርልኝ፣ ከእንግዲህ አልወልድም

ስትል የአማራ እናት አንጎራጎረች።

የአዲሱ ጣልያን ፈጠር ትርክት ሰላባ ትውልድ፣ 1966 ዓ.ም አቢዮት ሲያፈነዳ የተነሳበት ድደነ ትርክት መሰረተ እርሾው የፖለቲካ ፍልስፍና ዝንፈት፣ ሸዋራራነት ስለገጠመው ከተማ እና ከተሜነትን፣ ሀብት እና ባለሀብትን፣ ታሪክ እና ሀይማኖትን እንደ ጠላት ቆጥሮ ሊዋጋቸው ሲነሳ… የእምነት፣ የጥበብ፣ የታሪክና ትውፊት ማዕከለ ተቋማትም ኢላማ ሢደረጉ…  አዲስ አበባም  የትላንት መንግስተ ታሪክ ማዕከል ነችና የአዲሱ ትውልድ አብዮት ፍንዳታ ስሁት ፅንሰ እሳቤ አመክንዮ አጥፊው ነድ፣ ታሪካዊ አደጋ ከደቀኑባቸው እድሜ ጠገብ የፖለቲካ ማዕከላት አንዷ ሆነች።

የደርግ፣ ሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም ለአዲስ አበባ እና አዲስ አበቤ ይዞት የመጣው ሳንካ

ክፍል .2 ይቀጥላል…

የጃንሜዳ ቲዩብ መስራች እና ጋዜጠኛ ሰሎሞን ጌታቸው ከ UK

jornalist Solomon Getachew

Discover more from wenchifEthiopia.com ወንጭፍ ኢትዮጵያ

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading