ትግሉ የማን ነው?

ትግሉ የማን ነው?

(የፋኖ ገሚስ ችግርና መፍትሔዎች ትንታኔ)

(ጌጥዬ ያለው) #እንደ መግቢያ

ታሪክ የአማራ የፖለቲካ ካፒታል ነው። የዘመናት መፈክራችንም “አማራ ታሪኩን ያድሳል” የሚል ነበር። ነውም። ታሪክ ሦስት መሰረታዊ ጠቀሜታዎች አሉት። እነርሱም ትናንትን ማወቅ፣ ዛሬን መገንዘብ እና ነገን መተንበይ ናቸው። ያለ ታሪክ የፖለቲካ ትንተና እምብዛም ነው። ያለትንታኔ የፖለቲካ ሥራም ሆነ ትግል ደግሞ ዳጥ የበዛበት የሌሊት ጉዞ እንደማለት ነው። ታዲያ ባለታሪኩ አማራ ከታሪኩ ካለመጠቀሙም በላይ ትናንት አባቶቹ ያለፉበትን ችግር እየደገመ ይመስላል። ‘ስትሄድ ያደናቀፈህ ድንጋይ ስትመለስ ከደገመህ እንቅፋቱ አንተ ነህ’ ይሉት አማራዊ ብኂል በእኛ ላይ ገቢራዊ እየሆነ ነው። ነገራችን ሁሉ ‘የእሳት ልጅ አመድ’ እንደምንለው ከመሆኑ በፊት ማጤን ያለብን ጉዳዮች አሉ። በመሆኑም በዚህ መጣጥፍ ውስጥ የአማራ ፋኖ እየገጠሙት ካሉ ሰሞነኛ ችግሮች አኳያ ከታሪክ ሊማራቸው የሚገቡ ነጥቦችን እንዳስሳለን። ከጎረቤቶቹ ብሎም ከአለም ተሞክሮ ሊያጤናቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች እናትታለን። ለመሆኑ ፋኖ በሁለት ዓመታት የስሉ ውጊያ እንቅስቃሴው ግዙፍ ጣጣ የሆነበት ምንድን ነው? እንዳሻው አላዘልል ያሉት ሰሞነኛ ሆድ ቁርጠቶቹ ምን ምንድን ናቸው? #የፋኖ ጣጣዎች

የአማራ ፋኖ ካሉበት መሰናክሎች መካከል እንደ ተከቭ ወድሮ በመያዝ አላራምድ ያለው የአንድነት ጉዳይ ነው። በአንድ የዕዝ ሰንሰለት ስር የሚከተት ሁለንተናዊ አመራር አልፈጠረም። ከብዙ ድካም በኋላ የተመሰረቱት ሁለቱ ድርጅቶች ማለትም ከአንድ አመት በፊት የተቋቋመው የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) እና የአማራ ፋኖ ብሄራዊ ኃይል (አፋብኃ) ይቀራረባሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር። አንድ ቀን አፍንጫቸው ስር የሰፈረ ከንቱ ኩርፊያ ይከላል ተብሎ ተገምቶ ነበር። ከአመራሮቹ የእርስ በራስ ርግጫ አንፃር አንድነታቸውን በቀላሉ ባንጠብቅም ስንኳ ፍቅራቸውን ተመኝተን ነበር። ሆኖም የአማራ ምድር እጸ መስተዋድድ የደረቀበት መስሏል።

ቢቻል እንደ ውሃ እና ወተት ይዋሀዳሉ፣ መሀዋድ ባይችሉ እንደ ውሃ እና ዘይት ጎራቸውን ለይተው ጨልጣ ልትጠጣቸው የምትሻንም ሆነ የምትደፋቸውን ድመት፣ ከሁሉም በላይ የጋራ ዋንጫቸውን የሚያቃጥልን ዘረ ፈጅ ሰደድ እሳት በቅንጅት ወይም በትብብር ያጠቃሉ ተብሎ ታስቦ ነበር። ይህ መሆን ባይችል ስንኳ እርስበርስ እንዳይዋጉ የአማራ ሕዝብ ድርብርብ ፍላጎት ነበር። ሆኖም ተዋጉ። አንዱ ሌላውን በሰላማዊ ፖለቲካዊ ሂደት መታገል ሲችል እርስ በራስ መዋጋት አንገት የሚሰብር ስህተት ነው። ይህ ስህተት ዛሬ በአማራ ሕዝብ ፊት፣ በብዙሃኑ ተዋጊ ሰራዊት ፊት፣ በፖለቲካ መድረክ፣ በሞራል ልዕልና ፊት የሚያሳፍር ነው። ነገ ደግሞ በታሪክ ገጽ የሚያሸማቅቅ ይሆናል። ጀግናውን አርበኛ ተራ ነፍሰ ገዳይ፣ ወንጀለኛ የሚያደርግ ነው። የጠላትን ምሽጎች የሰባበረ ጀግና “የአርበኛ ከፍያለው ደሴ ገዳይ” የሚል ካባን ይደርባል። ሽመል ታጥቆ ዲሽቃ የማረከ የጦር ገበሬ “ኮሎኔል ጌታሁን መኮነንን ከጀርባ የወጋ ባንዳ” የሚል ጋቢን ከወደቀበት አንስቶ ከእነትቢያው ይጎናነባል። ይህ በአርበኞች ታሪክ ላይ የእርስ በራስ ውጊያ የሚዘራው አረም ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሁለቱ ድርጅቶች እርስ በራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለየብቻቸውም በአባሎቻቸው መካከል መጋጨት ጀምረዋል። #አፋብኃ

የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል (አፋብኃ) በአፋሕድ ምስረታ ወቅት የግል ጥቅማቸው የተነካ የመሰላቸው አኩራፊ አደረጃጀቶች ስብስብ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በየጠቅላይ ግዛቶቻቸው አንድ ዕዝ ወይም ንዑስ ድርጅት ለማቋቋም በነበረው ሂደት በሥልጣን፣ በጦር መሳሪያ እና ፋይናንስን ጨምሮ በሎጀስቲክ ክፍፍል የተኳረፉ ክንፎች ፍንካቻቸው በተገኘበት ላለመገኘት ሲዋልሉ የተሰባሰቡበት ማዕቀፍ ነው። ድርጅታዊ ቅርፅ የለውም። መዋቅራዊ ሰንሰለት የለውም። የሚመራበት የፖለቲካ ማኔፌስቶ የለውም። አራት የተለያዩ ድርጅቶች በመተባበር እና ከመካከላቸው በተውጣጡ 13 የማዕከላዊ ዕዝ የጋራ መሪነት የሚታገል ስብስብ ነው። ስለዚህ ትብብር ወይም ቅንጅት እንጂ ወጥ ድርጅት ልንለው አያስደፍርም። የሕዝቡ፣ የሰራዊቱ እና የራሳቸው የመሪዎች ፍላጎት ወጥ ድርጅት መፍጠር ሆኖ ሳለ ይህ እንዲሆን የጋበዘው ከ13ቱ መካከል ጠቅላይ መሪ የሚሆን አንድ ሰው መሰየም ስላልተቻለ ነው። ለዚህ ዋነኛው ምክንያት የስልጣን ሽኩቻ ነው። አንዱ በአንዱ ለመመራት ፈቃደኛ አለመሆናቸው ነው።

የድርጅት ምስረታው ሲታሰብ አርበኛ ዘመነ ካሤ መሪ ሆኖ እንደሚመጣ ተገምቶ ነበር። ሆኖም ለአሳው የዘረጋው መረብ ራሱን ጠርንፎ ባሕር ውስጥ ዶለው። ጉዳዩን ጥቂት እናፍታታው:-

በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት ምስረታ ወቅት የድርጅቱ መሪ ለመሆን በነበረው ፉክክር ዘመነ በተሳታፊዎቹ የአብላጫ ድምፅ በአርበኛ እስክንድር ነጋ ተቀድሞ የሁለተኝነት ደረጃን ያዘ። ሆኖም ይህን በፀጋ አልተቀበለም። ‘ጎጃሜ ስለሆንኩ ተገፋሁ’ የሚል ቅስቀሳን አስተጋባ። ሳይታወቀው ይመስለኛል ራሱን ከአማራ ብሔርተኝነት አውርዶ ወንዘኝነት ውስጥ ፈጠፈጠ። ይህ አስቀድሞ በ-ብአዴን በኩል ሲቆሰቆስ የነበረውን የከፋፍለህ ግዛው ማለትም የ“ጎጃም – ጎንደር” የመንደርተኝነት እንቅስቃሴ ፍም ሆኖ ውስጥ ውስጡን ሞከሞከው። ይኸው አስተሳሰብ የአማራ ፋኖ በጎንደር አንድነትን ወክሎ በድርጅት ምስረታው ላይ በተገኘው በአርበኛ ሐብቴ ወልዴ አንደበት ተገልጦ የጉባዔ ወንበር ይዞ ጉች አለ። አርበኛ ዘመነ ካሤ የድርጅቱ መሪ እንዲሆን ሲታጭ አርበኛ ሐብቴ “ዘመነ መሪ የሚሆን ከሆነ ሰራዊቴ በብስጭት ይበተንብኛል። የእርሱን መሪነት የእኛ ሰራዊት አይቀበልም” አለ። ይህ ለመናገር ቀርቶ ለመስማት ስንኳ የሚቀፍ ቢሆንም በሱዳኑ ጉባኤ ከፍ ብሎ ተነገረ። ተደመጠም። በነገራችን ላይ እነርሱ “የቋራ ቃል ኪዳን” ቢሉትም ሱዳን ሳምሪ በተባለው የወያኔ ጦር አጃቢነት መሰብሰባቸው ይታወሳል።

ከዚህ ቀጥሎ ጀኔራል ተፈራ ማሞ ለመሪነት ታጨ። ተፈራ የድርጅቱ መስራች ሆኖ የገባው የየትኛውንም ጠቅላይ ግዛት ዕዝ ወክሎ አይደለም። የሕይዎት ዘመን ወታደራዊ ልምዱን፣ ለአማራ ሕዝብ ትግል ያደረጋቸው አበርክቶዎችና አሁንም በጦር ግንባር መገኘቱን ሚዛን ላይ በማስቀመጥ በልዩ ሁኔታ ራሱን ችሎ ነው የገባው። ይህ የመንደር ውክልናን አስቀርቶ ማንኛውም ታጋይ በአማራነቱ እና በችሎታው እንዲመዘን ለማስቻል ፈር ቀዳጅ ነው። ከዚህ አንፃር አፋብኃ የወሰደው ርምጃ ያስመሰግነዋል።

ወደ ምርጫው ሂደት እንመለስ። የጀኔራል ተፈራ መሪነትም ቅቡልነት አላገኘም። ጉባዔተኛው ቢተክለው ስንኳ ሠራዊቱ እና ሕዝቡ የሚነቅለው መሪ ማይሆንባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ። ቢያንስ የተአማኒነት እና የፖለቲካ ብቃት ጥያቄዎች ይነሳሉ። ሆኖም እዚህ ድረስ ሳይደከም “ማናችሁም እኔን ለመምራት ብቁ አይደላችሁም። እስክንድር አይመራኝም ብየ መጥቼ በእናንተ አልመራም” በማለት ዘመነ ድካሙን አሳጠረው። በርግጥ እዚህ ላይ ዘመነ እውነት ያለው ይመስለኛል። ለዚህም ሁለት ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፦

1-የአማራ ሕዝብ ነባሪ መሪ (Default Leader) ሆኗል። ጉባኤ ቢመርጠው ወይም ባይመርጠው ትግሉ ራሱ መሪ አድርጎታል። ይህም ማለት በትግሉ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴው በሕዝብ ልቦና ውስጥ እንደ መሪ እየታሰበ ነው ማለት ነው። በመገናኛ ብዙሃን መሪዎች ሲጠቀሱ ማጣቀሻ ተደርጎ ስሙ የሚነሳ ነው። እንደ መሪ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። የፖለቲካ ተሳታፊም ነው። ወደ ሌሎቹ ስንመጣ ፖለቲካው ውስጥ አሉ እንጂ ንቁ ተሳታፊ አይደሉም። ባሕሩ ውስጥ አሉ እንጂ አይዋኙም። ነገሩን በተማሪዎች መማሪያ ክፍል ብንመስለው ዘመነ ስህተትም ይሁን ትክክል በተደጋጋሚ እጁን እያወጣ የሚሳተፍ፣ ከአስተማሪው ጋር አብሮ የሚተጋ ተማሪ ነው። ሌሎቹ ደግሞ ተሳትፎ አልቦ ናቸው። የፖለቲካ ስብዕናቸውን እምብዛም አናውቀውም። ሲወድቁ እና ሲነሱ አላየንም። አንዳዶቹ ‘ጥሩ ምሁራዊ ቅርበት አላቸው፣ ፖለቲካ ይረዳሉ፣ ስለድርጅታዊ አመራር ግንዛቤ አላቸው’ የሚባሉ ተወዳዳሪዎች ችሎታው እንዳላቸው ቢታመንም ትግሉን ግማሽ መንገድ ላይ የተቀላቀሉ በመሆናቸው ገና አልተፈተኑም።

2-አፋብኃ-ን የመሰረቱት ስብስቦች ሁሉም በአፋሕድ ምስረታ ውስጥ የተሳተፉ ናቸው። አፋሕድ ላይ በነበረው ውድድር በዘመነ በይፋ ተበልጠዋል። መበለጥ ብቻ ሳይሆን ከሀብቴ በስተቀር ራሳቸውም እጃቸውን አውጥተው መርጠውታል። (ሐብቴ ከአፋሕድ ወጥቶ ወደ አፋብኃ የተቀላቀለ መሆኑን ልብ ይሏል)

ስለዚህ ትናንት የመረጡትን ዛሬ ላይመርጡ የሚችሉበት ምክንያት እምብዛም አይታይም። በምክንያትነት የሚከተሉትን ልንጠቅስ እንችላለን፦
1- የአዲስ ገቢው የተፈራ ማሞ መኖር

ከዚህ አኳያ ከላይ በጠቀስናቸው እና በሌሎችም ምክንያቶች ከዘመነ የሚበልጥ ስላልሆነ ዉሃ የሚያነሳ ምክንያት አይመስለኝም።

2- ሌሎቹ ተፎካካሪዎች ‘ባለፈው አንድ አመት ውስጥ ከፍተኛ ልኅቀት አሳይተን ዘመነን በልጠነዋል’ የሚሉ ከሆነ (የዚህን ፍርድ ለአንባቢ ትቸዋለሁ)

3- ‘እኛ እድገት ባናሳይም ዘመነ ውድቀት አሳይቶ ወደ ኋላ ተመልሷል’ ብለው የሚያስቡ ከሆነ

ይህን በተመለከተ ዘመነ ወደ ኋላ ከመመለስ ይልቅ እንዳውም ወደ ፊት ተስፈንጥሯል ማለት ይቻላል። የድርጅቱን መስራቾች ወደ አንድ ማዕቀፍ ለማምጣት የሰባሳቢነት ሚናን ተጫውቷል። የአጋሩ ማንነት የሚያስተች ቢሆንም አጋር ፍለጋ ባደረጉት ጥረትም የመሪነት ሚናን ተጫውቷል። ከእስክንድር ጋር የገባበት እንካሰላንትያም ከእነድክመቱም ቢሆን የፖለቲካ ተሳትፎዉን አሳድጎታል። የእስክንድር አብዝቶ አለመመላለስም ጠቅሞታል።

ከተዘረዘሩት ሁሉ የባሰው ችግር ሰሞኑን የመጣው ነው። አማራ ፋኖ በጎጃም ከአፋብኃ ተገንጥሎ ወጥቷል። ይህ ዘመነን ብቻ ሳይሆን የአማራ ፋኖ በጎጃም አመራሮችን በጠቅላላ ከሕዝብ እና ከሰራዊቱ ጋር የሚያፋጥጥ ነው። ከቀሪው አማራ የተነጠለ እና ዙሪያውን በአባይ የታጠረ ትግል መዘዙ ከባድ ነው።

በሌላ በኩል አፋብኃ እነ ዘመነን ትቶም ሰላም አይሆንም። እዚህም ውስጥ የመሪነት ጉዳይ ሲመጣ ሽኩቻው መቀጠሉ አይቀርም። በቅርቡ ከእስር ቤት የወጣውን አርበኛ ሔኖክ አዲሴን እና ጀኔራል ተፈራን ማሻኮት ተጀምሯል። ሽኩቻው ላይ ሐብቴ ወልዴም መጨመሩ አይቀርም። ‘ኃይል የለህም’ በሚል ሒስ ከሽኩቻው ውጭ የሆነው አርበኛ ደሳለኝ ሲያስብ ሸዋ ነው። እርሱ ሁሉም ጉባዔዎች ላይ ከመስማማት የዘለለ ዕድል የለውም።

በአጠቃላይ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል ተቋም ሆኖ የመቀጠል እጣው እንደ ቀጭን ክር የመነመነ ነው። ይልቁንም የአማራ ብሔርተኝነትን አጥፍቶ ጎጠኝነትን የማንበር ዕድሉ እንደ ጮቄ ተራራ የተገማሸረ ነው። ይህም የአማራን ተስፋ እንደ ጮቄ ብርድ ቀፍድዶ የሚያኮማትር ነው። #አፋሕድ

የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት የተቋም ቅርፅ ያለው ድርጅት ነው። አንድ መሪ አለው። የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች አሉት። ከሰብሳቢው ጀምሮ ወደ ታች የሚወርዱ ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ የሕዝብ አስተዳድር እና የረባ ሥራ ባይሠሩም የውጭ ሀገር አደረጃጀት መዋቅሮች አሉት። በይፋ የጸደቀ ባይሆንም የሚመራበት የፖለቲካ ማኔፌስቶ ረቂቅ አለው። በመሆኑም ከመዋቅር አንፃር የተስተካከለ ተቋም ነው።

ነገር ግን ከድርጅቱ ይልቅ መስራች ዕዞቹ ሉዓላዊ መስለው ይታያሉ። በጉባዔ የተወሰነ ባይሆንም ከድርጅቱ በላይ በየነፃ ቀጣናቸው ከፍተኛ ስልጣን ያላቸው ዕዞች ናቸው። በሀገር ውስጥ ከሕዝብ ገንዘብ የመሰብሰብ፣ ሕዝብን የማስተዳደር፣ ሰራዊቱን የመምራት፣ የማሰልጠን፣ የማስታጠቅ፣ የመዋጋት ስልጣን ከአፋሕድ በላይ ይዘው ይታያሉ። በርግጥ በአንድ አመት ሂደት ውስጥ የተሻሻሉ ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ ከዚህ ቀደም ዕዞች በውጭ ሀገር በይፋ ከሕዝብ ገንዘብ ይሰበስቡ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህን ስልጣን ለድርጅቱ ብቻ እየለቀቁ ይመስላል። በአጠቃላይ ከሕዝባዊ ንቅናቄ ወደ ድርጅታዊ አሰራር እየገቡ ነው። ጉዞው አዝጋሚ ቢሆንም በጥሩ ጎዳና ላይ ናቸው።

በአንፃሩ አስነዋሪው የስልጣን ሽኩቻ አሁንም ቀጥሏል። የድርጅቱ አመራሮች የትግል አፈፃፀማቸውን ገምግመዋል። በዚህም “ድርጅቱ ተንቀራፏል። ድክመት አሳይቷል” በሚል ተስማምተዋል። የድክመቶቹን ባለቤት በተመለከተ በሁለት ጎራ ተከፍለዋል። አንደኛው ጎራ ድክመቱን ሸክፎ ለመሪው አርበኛ እስክንድር ነጋ አሸክሞታል። እርሱም በየጊዜው “ሓላፊነቱን እወስዳለሁ” ማለት ይቀናዋል። መፍትሔውም እስክንድርን በሌላ መሪ መተካት እንደሆነ ይከራከራል። ይህንኑ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር። ሆኖም በውጭ ሀገር በሚገኙ ታጋዮች በኩል ተቃውሞ ስለገጠመው ለጊዜው ባለበት ቆሟል። ጊዜ ጠብቆ መነሳቱ የሚቀር አይመስልም።

ሌላኛው ጎራ የችግሮችን ምንጭ የሥራ ስፈፃሚ ኮሚቴውን አድርጎታል። መፍትሔ የሚለውም መሪውን ጨምሮ ሁሉም የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በየተመደቡበት ዘርፍ ተግተው እንዲታገሉ ማድረግን ነው። ‘የየዘርፍ ድክመቶች ይለዩና እነርሱ እንዲስተካከሉ ጥረት ይደረግ’ ባይ ነው። በተለይ በዚህ ሰዓት እስክንድርን ከሓላፊነት ማንሳት ለከፋ ቀውስና ድርጅታዊ ፍርሰት እንደሚዳርግ ያስባል።

ይህ ስምምነት ያላገኘ ጉዳይ ነው።

ድርጅቱ ውስጥ ብአዴን ሰርጎ መግባቱን ራሱ አፋሕድ በአንድ መግለጫው ይፋ አድርጓል። ድርጅቱን ከአብይ አሕመድ የወረራ አገዛዝ ጋር ተደራዳሪ ብሎም ተንበርካኪ ለማድረግ እየሰራ ያለ ቡድን መኖሩ እሙን ነው። ይህ ቡድን ከፍተኛ የውሳኔ ሰጭነት ደራጃ ላይ መቀመጡም አሳሳቢ ነው። በመሆኑም ድርጅቱ የአብን እጣ ፋንታ እንዳይገጥመውና የአማራን ሕዝብ ጥያቄ ሜዳ ላይ በትኖ የአገዛዙ ወሽመጥ እንዳይሆን ስጋት አለ። በተለይም የድርጅቱ ሰብሳቢ ከሓላፊነት ከተነሳ ይህ የመሆን ዕድሉን ይጨምረዋል። በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ውስጥ ሽግሽግ በሚል በለጠ ሞላ፣ ደሳለኝ ጫኔን (ዶ/ር) ተክቶ በመምጣት ንቅናቄውን የጠላት አገልጋይ ያደረገበት ታሪክ እንዳይደገም ያሰጋል። እዚህ ላይ የአፋብኃ-ን ከወያኔ ጋር መለጠፍ ስንጨምርበት የአማራን እናት የወላድ መካን ያደርጋታል።

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ከሀገር ውጭ የተቋቋመው የአፋሕድ ኮሚቴ ከሁለት ተሰንጥቋል። ከመሰንጠቁ በላይ ለስንጠቃ ያበቁት ምክንያቶች አሳሳቢ ናቸው። ነገሩ እንዲህ ነው፦

የውጭ አስተባባሪ ኮሚቴው አባላት ሁለት አይነት ንዑስ የፖለቲካ መሰረት ያላቸው ናቸው። የመጀመሪያዎቹ የድርጅቱን መስራች ዕዞች ወክለው የተሰየሙ ሲሆን የጎንደር፣ የሸዋ እና የቤተ አማራ ዕዞችን ይወክላሉ። ሌላኞቹ ከአፋሕድ መስራቾች መካከል አንዱ የሆነው ማለትም እነ አርበኛ እስክንድር ነጋ እና ካፕቴን መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ይዘውት የቀረቡት የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ሰራዊትን ወክለው ኮሚቴው ውስጥ የሚሳተፉ ናቸው። የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ሰራዊት ከመርህ አኳያ ማንኛቸውንም አማሮች ያማከለ ድርጅት ሲሆን በይፋ ያዋቀረው ግን የጎጃም ዕዝን ብቻ ነው። ታዲያ በኮሚቴው የስልጣን ክፍፍል እና የአባላት መጠን ድልድል ላይ የኮታ ሽኩቻዎች ተፈጠሩ። ይኸውም የሌሎች ዕዞች ወኪሎች ለእያንዳዳቸው ሁለት ቢሆንም ከጎንደር ዕዝ በኩል በኮሚቴው የሚሳተፉ ወኪሎቻቸው አራት እንዲሆኑላቸው ጠየቁ። ለዚህም ሁለት ምክንያቶችን አቅርበዋል፦

1- ድርጅቱ ሲመሰረት በጎንደር ሁለት ዕዞች ነበሩ። መስራች ዕዞች ለእያንዳዳቸው በውጩ ኮሚቴ ሁለት ወኪል እንዲኖራቸው ስለተደገ፣ በሀገር ቤቱ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴም ውክልናቸው እንዲሁ ስለነበረ ጎንደር አራት ወኪሎች ነበሩት። ቆይቶ ግን በሀብቴ ወልዴ የሚመራው አንዱ ዕዝ ከአፋሕድ ወጥቶ በመሄዱ የጎንደር ውክልናም አነሰ። ይህ መጠነኛ ውዝግብ አስነስቷል። በአንድ በኩል እንደከዚህ ቀደሙ ውክልናችን አይቀነስ የሚል ሲሆን በሌላ በኩል ‘ውክልናችሁ በፊትም ይኸው ነው። አሁንም አልተቀነሰም። የወከልነው ዕዞችን ነው። ሐብቴ የሚመራው ዕዝ አባል በነበረ ጊዜ ተወከለ። በተገነጠለ ጊዜ ደግሞ አይወከልም’ የሚል ነው።

2- ሌላኛው ጎንደር ከሌላው የበለጠ የቆዳ ስፋት ስላለው የበለጠ ውክልና ያሻዋል የሚል ነው። የዚህ ኃሳብ አቀንቃኞች በማህበራዊ ሚዲያ እንደማስረጃ የሚጠቅሱት ጠላቶቻችን የፌዴራል ስርዓቱን ሲያዋቅሩ ጎንደርን በአምስት ዞኖች መሸንሸናቸውን ነው። ደቡብ ጎንደር፣ ሰሜን ጎንደር፣ ምዕራብ ጎንደር፣ ማዕከላዊ ጎንደር፣ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ በማለት ይቆጥሯቸዋል። ሌሎች የአማራ ግዛቶች በዞን ብዛት ከዚህ ያነሱ መሆናቸውንም በንፅፅር ያቀርባሉ።

ይህ የውክልና ጥያቄ በሌሎቹ በኩል በተለይም የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ሰራዊትን ወክለው በውጭ በተቋቋሙት ዘንድ ተቃውሞ ገጠመው። ምክንያታቸውም በዕዞች መካከል ታናሽ እና ታላቅ የለም የሚል ነው።

በሌላ በኩል የሕዝባዊ ሰራዊቱ ወኪሎች “አስቀድሞ በሰሜን አሜሪካ ብዙ አደረጃጀቶች ስለፈጠርን የበለጠ መወከል አለብን” ይላሉ። በእነርሱ ዘንድ የየዕዞቹ ወኪሎች በጎጠኝነት ሲፈረጁ በአንፃሩ የዕዝ ወኪሎች የሕዝባዊ ሰራዊቱ ወኪሎችን ‘አማራነታቸው ያልተረጋገጠ፣ ከክልሉ ውጭ የመጡ’ በማለት ይጎነትሏቸዋል። እነኝህ ኃሳቦች ብዙ ጊዜ በጎንዮሽ ውይይቶች እና በማሕበራዊ ሚዲያ እየተንሸራሸሩ ናቸው። አልፎ አልፎ ደግሞ ተኳኩለውም ቢሆን በጉባዔ ይነገራሉ። ከመነገርም በጎጃም የነበረው የሕዝባዊ ሰራዊቱ አደረጃጀት ፈርሶ ስሙ ተለውጧል። በውጭ ያሉት ሙሉ በሙሉ ተገልለዋል።

መሪው አርበኛ እስክንድርን ጨምሮ አፋሕድ ከአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ሰራዊት ወኪሎች ውጭ የሆነ አዲስ የውጭ ኮሚቴ አደራጅቶ ወደ ተግባር አስገብቷል። ይህ ነው ልዩነቱን ወደ መግለጫ ንትርክ ያስገባው። የውጩ አደረጃጀት ደጋፊ በመሆኑ የአፋሕድ ሥራ አስፈፃሚ የወሰነውን ተቀብሎ የመሄድ ግዴታ እንዳለበትም ተነግሮታል። ሆኖም ውዝግቡን የበለጠ አንሮታል። ከውዝግቡ መሀል የሚነሱ ሃሳቦች በአንድ በኩል ‘ትግሉ የእኛ ነው። የእናተ አይደለም። እኛ ታጋይ፣ እናንተ ደጋፊዎቻችን ናችሁ’ የሚል እንድምታ ተሰጥቷቸዋል። በሌላ በኩል ‘እኛን የምትፈልጉን ለገንዘባችን ብቻ ነው። ለትግሉ ቤተሰባችንን ጎድተናል። ዋጋ ከፍለናል’ የሚሉ መስቃ ያዘሉ መከራከሪያዎች አሉ።

እነኝህ ውዝግቦች ዛሬ ካነሱት አቧራ ይልቅ ወደ ፊት የሚፈጥሩት ማዕበል አማራን የሚበትን ነው። ከትግሉም በዘለለ የአማራን ሕዝብ ኗሪ እና ስደተኛ፣ በመስተዳድሩ ውስጥ ያለ እና ከመስተዳድሩ ውጭ ያለ በሚል እንዳይከፋፍለው ስጋት አለኝ። ጎጠኝነት ገንግኖ የአማራ ብሔርተኝነት እንዳይከስም ያሰጋል። ይህ እንዳይሆን ትግሉ የእኛ ነው. . . የእኛ ነው. . . ከመባባል ወጥቶ። ‘እኛ አማሮች ነን። ትግሉም የአማራ ነው። ጎጃም፣ ጎንደር፣ ቤተ አማራ፣ ሸዋ . . . የትግል ግንባሮች እንጂ ማንነቶች አይደሉም። ማንነታችን አማራ ነው’ ብሎ ማሰብን ይጠይቃል። እንደ እስራኤላውያን በማንኛውም የአለም አፅናፍ ያለ አማራ በአማራነት ጥላ ስር መሰባሰብ አለበት። #ታሪካዊ ተሞክሮዎች

በአምስት አመቱ የጣልያን ወረራ ጊዜ ከድል መልስ አራት የተለያዩ አሰላለፎች ነበሩ። እነርሱም፦

1- የተዋጊ አርበኞች አሰላለፍ
2- የውስጥ አርበኞች አሰላለፍ
3- የስደተኛ ተሟጋች አርበኞች አሰላለፍ
4- የባንዳዎች አሰላለፍ ናቸው። (ክፍል 2 ይቀጥላል . . .)

Discover more from wenchifEthiopia.com ወንጭፍ ኢትዮጵያ

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading