ታንቆ ከመሞት እየታገሉ መሞት አይሻልም?

ከሞቱ አይቀር እየታገሉ አይሻልም?
………………………………………..
ሞገድ እጅጉ
ጠበቃ አንዱዓለም በዕውቀቱ ትናንት በማህበራዊ ገጹ አንድ አስደንጋጭ ዜና ለጥፎ ነበር፡፡ ይሄውም፤ ከአብይ አህመድ አፍንጫ ሥር፤ አቧሬ አንድ አባት ራሳቸውን ማጥፋታቸው ነው፡፡ የጠበቃው ሀሳብ ሲጠቃለል እንዲህ ነው፡፡
73 ዓመታት የኖሩበት አካባቢያቸውና ቤታቸው ሊፈርስ ሲሆን ለጠበቃው አመለከቱ፡፡ ጉዳዩን ይዞ እየተሯሯጠ ሳለ አፍራሹ ኃይል ቀድሞ ማፍረስ ጀመረ፡፡ ይህኔ እኚህ አባት በማምሻ ዕድሜያቸው ረሳቸውን አጠፉ፡፡
ዛሬ ጠዋት ደግሞ በአሃዱ ሬዲዮ 94.3 ይህ ዜና ተሰማ፡፡ ለኮሪደር ልማት ሲባል ቤታችሁ ሊፈርስ ነው ውጡ ተባሉ፡፡ ዕቃቸውን እንኳን አስተካክለው ሳያነሱ አስወጧቸው፡፡ የተለቀቀው ቤት ግን ወዲያውኑ ሌሎች ሰዎች እንዲገቡበት ተደረገ፡፡ ‹‹ምነው?›› ብለው ሲጠይቁም፤ ልቀቁ ከተባላችሁ መልቀቅ ነው የሚል የቁጣና ግልምጫ መልስ ተሰጣቸው፡፡
የአብይ አህመድ ኢትዮጵያ ይህን ትመስላለች!
አብይ አህመድ ባለፈው ዓመት ሲናገር፤ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር አለ እያላችሁ የምታወሩት የጠላት ወሬ ነው፤ ኢትዮጵያን ማለት ከፈለጋችሁ የእኔን ጎረቤቶች አቧሬ መጥታችሁ ማየት ትችላላችሁ›› ብሎ ነበር፡፡ ኢትዮጵያን የምታክል ትልቅ አገር በአንዲት መንደር ወክሎ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ አሾፈ፡፡ እውነታው ግን የአብይ አህመድ ኢትዮጵያ እነሆ የዛሬዋን አቧሬ ትመስላለች፤ ራሳቸውን የሚያጠፉባት ሆናለች፡፡
የአብይ አህመድ አገዛዝ ‹‹የኮሪደር ልማት›› እያለ በሚጠራው የጥፋት ዘመቻ ራሳቸውን ያጠፉ ሰዎች ከዕለት ወደ ዕለት ቁጥራቸው እየጨመረ ነው፡፡ በየዕለቱ የሚሰማው ዜና ራሳቸውን አጠፉ የሚል ነው፡፡ የሚይዙት የሚጨብጡት ሲጠፋቸው፣ አቤት የሚሉበት የህግ አካል ሲቸግራቸው፣ ‹‹የህግ ያለህ›› የሚሉበት የፀጥታ አካል የጥፋቱ ተባባሪ ቢሆንባቸው፣ ሰማይ ቢደፋባቸውና የሚያደርጉት ቢቸግራቸው፤ የመጨረሻ አማራጫቸውን ራሳቸውን ማጥፋት አደረጉ፡፡ እነሆ የአገዛዙ ቋሚ ሥራ ከሰማይ በድሮን፣ ከምድር በስናይበርና በድሽቃ፣ የቀረውንም ሕይወቱን እንዲጠላና ራሱን እንዲያጠፋ ማድረግ ሆነ፡፡
እዚህ ላይ ግን አንድ አስገራሚ ነገር አለ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን የሕዝቡ ስነ ልቦና አሁንም አልነቃም፡፡ ይህ የሚያሳየው የማህበረሰባችን የንቃተ ህሊና ደረጃ ገና ብዙ እንደሚቀረው ነው፡፡ የአብይ አህመድ ሥልጣን ከፈጣሪ የመጣ ነው ብሎ የሚያምን አለ ማለት ነው፡፡ ከፈጣሪ ውጭ ማንም ምንም ሊያደርገው አይችልም ተብሎ ይታመናል ማለት ነው፡፡ ልክ ምንም ማድረግ እንደማይቻል አንዳች ሰማያዊ ቁጣ ይመስል ያለው ብቸኛ አማራጭ ራስን ማጥፋት እየሆነ ነው፡፡
በአዛውንቶች አይፈረድም፤ ቢያንስ ሥልጣን የፈጣሪ ነው ይባል በነበረበት ዘመን የኖሩ ናቸው፡፡ ለእነርሱ ቤታቸው የሚፈርስባቸው በአንድ መሃይም ግለሰብ የግል ፍላጎት ሳይሆን በፈጣሪ ቁጣ ነው ብለው ሊያምኑ ይችላሉ፡፡
እጅግ አሳዛኝ የሚያደርገው ግን የአገር ዳር ድንበር የመጠበቅ አቅም አለው የሚባለው ፈርጣማ ወጣት ቤቱ ፈርሶበት አስፋልት ዳር ሲያለቅስ ማየት ነው፡፡ የጥፋት ዘመቻው ከሚያልፍባቸው አካባቢዎች የተፈናቀሉ ወጣቶች በየዳርቻው የቆርቆሮ መጠለያ ውስጥ ተጥለዋል፡፡ እናቶችና አባቶች በአካላዊም ሆነ ስነ ልቦናዊ ባህሪያቸው ለቁጣ ሊነሱ አይችሉም፡፡ ብረት ሲገፋ የኖረ እና ጡንታቸውን ያፈረጠመ ጎረምሳ ግን ከአሮጊትና ሽማግሌ ጋር ሆኖ አብሮ ያለቅሳል፡፡ ደረቱን ሲያሰፋ የነበረው ከእንዲህ አይነት ወርዴት ራሱን ለመከላከል ሳይሆን ሴት ለማማለል ብቻ እንዲሆነው ነበር ማለት ነው፡፡
ወጣት ማለት በአካል ብቻ ሳይሆን በስነ ልቦናም ፈርጣማ መሆን አለበት፡፡ ወርዴትን ልክ እንደ አባቶቹ እምቢኝ ማለት አለበት፡፡ የውጭ ወራሪ አይደፍረንም ብለው እስከ 1000 ኪሎ ሜትር በእፍራቸው እየተጓዙ ክብራቸውን ያስጠበቁ እሳት የላሱ አባቶች፤ እንዲህ አይነት ውሃ የተደፋበት ልጅ ወለዱ፡፡
አሁን ያለው አገዛዝ ከጣሊያን ወራሪ የከፋ ነው፡፡ የጣሊያን ወራሪ ባሪያ ከሆንክለት አይነካህም፡፡ የአብይ አህመድ አገዛዝ ግን ባሪያ ሆነህለትም አይምርህም፡፡ ምክንያቱም የአገዛዙ ምኞት ከራሱ ብሄርና ሃይማኖት ውጭ የሆነውን ማጥፋት ነው፡፡ የውጭ ወራሪ ዓላማው ባሪያ አድርጎ መግዛት ሲሆን፤ የአብይ አህመድ ግን ዓላማው ማጥፋት ነው፡፡ ስለዚህ ይህን አገዛዝ ከቅኝ ገዥ በላይ መታገል ያስፈልግ ነበር ማለት ነው፡፡

በነገራችን ላይ ራሳቸውን ያላጠፉት ተፈናቃዮችም ጤነኛ ናቸው ለማለት አያስደፍርም፤ ብዙ የስነ ልቦና ጫና የደረሰባቸው ናቸው፡፡ ሰው ከሞቀ ቤቱ ወጥቶ ባደገበት አገር ላይ ሜዳ ላይ ሲጣል ጤነኛ ሊሆን አይችልም፡፡

ስለዚህ በስነ ልቦናም ሆነ በአካል በራስ ከመሞት እየታገሉ መሞት ይሻላል!

Discover more from wenchifEthiopia.com ወንጭፍ ኢትዮጵያ

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading