“የባሰ አታንጣ ይላል እግዚያብሄር ያነሳዋል ይላል”
………………………………………………….
ሞገድ እጅጉ
የኢትዮጵያ የሰራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን ፓርላማው ፍቃደኛ ከሆነ በስራ መውጫ ስዓት ፌስታል ይዘው ከሆቴል ተመላሸ ምግብ የሚለምኑ ሰራተኞች መኖራቸውን ማሳየት እንደሚችል መናገሩ ትናንት እና ዛሬ የማህበራዊ ገጾች አጀንዳ ሆኗል፡፡
ኮንፌዴሬሽን ይህን ያለው በቅርቡ ይጸድቃል ተብሎ በሚጠበቀው የፌዴራል ገቢ ግብር ማሻሽያ ረቂቅ አዋጅ ላይ የብልጽግና ተወካዮች ምክር ቤት ከፕላን በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከባለድርሻ አካላት ጋር ወይይት ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡
ብልጽግና የሙሉ ጊዜ ሥራው ዘረፋ እየሆነ ነው፡፡ አገሪቱ ውስጥ አለ ለሚባለው ችግር ሁሉ የሚያመጣው መፍትሔ እልህ እና ‹‹ምን ታመጣላችሁ?›› የሚል የእብሪተኝነት መልስ ነው፡፡ ይህን የዘረፋ አዋጅ ያወጣው ሕዝቡ በኑሮ ውድነት እየተሰቃዬ ነው የሚል ቅሬታ በቀረበበት ወቅት ነው፡፡ ለዚህ ቅሬታ ብልጽግና የሰጠው መልስ እንዲያውም ከመደበኛው ግብር ባሻገር ሌላ ተጨማሪ ግብር አስከፍላችኋላሁ የሚል ነው፡፡
ይህ ለምን ሆነ?
ሕዝቡ ምንም እንደማያመጣ አረጋግጧል፡፡ ቤት ከአናቱ ላይ ሲያፈርሱበት ዝም ያለ ሕዝብ፣ መንግሥት መግቢያ መውጫ አሳጥቶ፣ ጎዳና ላይም እንዳይኖር አድርጎ ሲያሳድደው ዝም ያለ ሕዝብ ግብር ተጨመረብኝ ብሎ ቅሬታ ሊያቀርብ አይችልም፡፡ እንዲህ አይነት ሕዝብ ለዘራፊ መንግሥት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ አሳዛኙ ነገር አገዛዙ መግቢያ መውጫ አሳጥቶ ሰማይ ምድር የተደፋባቸው ሰዎች የወሰዱት የመጨረሻው እርምጃ ራሳቸውን ማጥፋት ነው፡፡ ለዚህ ችግር የተዳረጉበት ምክንያት ሰው ሰራሽ ነው ብለው አላሰቡም ማለት ነው፡፡
ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ሲነገር እንደነበረው የመንግሥት ሠራተኞች የምሳ ሠዓት ላይ የሚበሉት አጥተው በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ይቆያሉ፡፡ የንግሥ በዓላት ሲኖሩ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ(ማስክ) አድርገው ሲለምኑ ታይተዋል፡፡ ከሆቴሎች ውስጥ ተመላሽ ምግብ ሲለምኑ ታይተዋል፡፡
በነገራችን ላይ ሆቴሎች ተመላሽ ምግብ እንዳይሰጡ በአገዛዙ ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገባቸው ነው፡፡ የአገዛዙ መንጋ ለሰዎች ጤንነት ሲባል ነው እያለ ሲያራግብ ነበር፡፡ አገዛዙ ይህን የሚያደርገው ግን ለዜጎች ጤንነት አስቦ ሳይሆን ለማኞች ተመላሽ ምግብን እንደ አማራጭ እንዳይጠቀሙ ነው፡፡ በምሬት ብዛት አዲስ አበባን ለቀው እንዲጠፉ ነው፡፡ ከረሃብ የከፋ ነገር እንደሌለ ግልጽ ነው፡፡ አብዛኛው የአገዛዙ ካድሬ ችጋር ሲያማቅቀው የኖረ ስለነበር ያውቀዋል፡፡ ዳሩ ግን ዛሬ የራሱን ከርስ ለመሙላት ሌላውን በረሃብ ማሳደድ የአገዛዙ ፖሊሲ ሆኖበታል፡፡
የዚህ ሁሉ ቀውስ ምክንያቱ ፍርሃት እና አላዋቂነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ሁሉ ቀውስ የተዳረገው በአንድ መሃይም አገር አጥፊ ምክንያት መሆኑነን አሁንም ልብ አላለም፡፡ የአብይ አህመድ የቅዠት ወንጌል ይሰበክ ዘንድ ሚሊዮኖች በረሃብና በጦርነት ማለቅ አለባቸው፡፡ የአብይ አህመድ የሥልጣን ጥማት ይቀጥል ዘንድ አገሪቱ እንዲህ መተራመስ አለባት፡፡
አገዛዙ ብቸኛ ገቢው ዘረፋ ነው፤ ምክንያቱም እንደ ሌሎች አገራት ወደ ውጭ የሚልከው ምርት የለውም፡፡ የአገሪቱ አምራች ኃይል ለማኝ ሆኗል፤ የአገሪቱ ለም መሬት የታንክ እና የዲሽቃ ምድጃ ሆኗል፡፡ ወደ ውጭ ይላኩ የነበሩ ምርቶች በአገር ውስጥም የማይመረቱ ሆነዋል፡፡ በብዙ የአገሪቱ አካባቢዎች ንግድ ቤቶች ፈርሰዋል፡፡ ስለዚህ ከነጋዴ የሚገኘው ግብርም ቀንሷል፡፡
ይሄ ሁሉ ሆኖ፤ በዝርፊያ የሚገኘው ገቢም የሚውለው ለጦርነት ነው፡፡ ሳር እና አበባ ለመትከል ነው፡፡ ለአንድ አበባ ብቻ በሚሊዮን ገንዘብ እንደሚወጣ በመንግሥት ተነግሯል፡፡ ስለዚህ መንግሥት ለሕዝብ አገልግሎት ለሚውሉ መሠረተ ልማቶች የሚያውለው በጀት የለውም፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያገናኝ አገር አቋራጭ መንገድ አይሰራም፤ በተቃራኒው ከዚህ በፊት የተሰሩ መንገዶችን ጦርነት ይዘጋል እንጂ!
ይህን አገር አጥፊና አገር አውዳሚ አገዛዝ እንደ ሕዝብ የተቃወመው መንግሥት የለም፡፡ አገዛዙ ይህን ስለተረዳ ይመስላል በሕዝቡ ላይ እየቀለደ ነው፡፡
አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ችግር አለው ብለው ሲያነሱ አገዛዙ የሚሰጠው መልስ ‹‹እናንተ አላችሁ እንጂ ሕዝቡ ችግር አለ አላለም›› የሚል ነው፡፡ ታዲያ ይፈረድበታል? ትክክል እኮ ነው፤ አሁንም ቢሆን ሕዝቡ አንጀቱን አሥሮ ሆዱን እያጮኸ በረሃብ ይቆላል እንጂ ችግር አለ አላለም፡፡ ሲከፋው የመጨረሻ አማራጭ ሲያጣ ራሱን አጠፋ እንጂ መንግሥትን መፍትሔ ፈልግ አላለም፡፡ ታዲያ ይሄን ሕዝብ አገዛዙ ቢቀልድበት ምን ይገርማል?
You must be logged in to post a comment.