
በአገዛዙ ፖሊስ በግፍ የተገደለውን የአዲስ አበባ ወጣት አስመልክቶ ከአዲስ አበባ ሚዲያ ምክር ቤት የተሰጠ አስቸካይ መግለጫ !!!
/
ግንቦት 1፣ 2018 ዓ.ም
/
የአዲስ አበባ ህዝብ በሟች ተገኝ ባልቻ ላይ የተፈፀመውን የግፍ ግድያ አደባባይ ወጥቶ መቃወሙ የሚደነቅ እና የሚደገፍ ነው !!!
/
በትላንትናው ዕለት፣ ማለትም፣ ዓርብ፣ ሚያዚያ 30፣ 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ፣ በተለምዶ “ሽሮ ሜዳ” ተብሎ በሚታወቀው ነባር ሰፈር በቤተሰቡ፣ በወዳጆቹ እና በማህበረሰቡ ዘንድ መልካም ስም የነበረው ታታሪው እና ታዳጊው ወጣት ተገኝ ባልቻ (ኦሮሮ) የከተማዋን ነዋሪ በጠላትነት እንዲመለከት የጥላቻ ትርክት በተጋተው የአገዛዙ ፖሊስ በአራት ጥይት በግፍ ተደብድቦ ለህልፈተ ህይወት ተዳርጓል። ሟች በግፍ የተገደለው በጠራራ ፀሃይ፣ “በህግ ቁጥጥር ስር” ሆኖ እና በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ነበር።
ሟች ወጣት ተገኝ ባልቻ፣ እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ የሀገር ባህል ልብሶችን በመነገድ ሰኬታማ እና ታዳጊ ነጋዴ ለመሆን በቅቶ የነበረ ቢሆንም፣ አገዛዙ በተለመደው የማፈናቀል ዘመቻው ተመጣጣኝ ምትክ ሳይሰጠው የንግድ ሱቁን አፍርሶ ንብረቱ በመጥፋቱ፣ ለከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራ የታደረገ የዘረኛው ሥርዓት ሰለባ ነበር።
ይህንን ተከትሎ፣ ከአንድ ወር በፊት “ሞተር ተራ” ተብሎ በሚጠራ የሽሮ ሜዳ አካባቢ በአንድ የአገዛዙ ፖሊስ አባል ተንኮሳ ሳቢያ ለእስር ተዳርጎ እንደነበር ታውቋል። ወጣት ተገኝ ታስሮ በነበረበት ወቅት አባቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን፣ በፖሊስ ታጅቦ በአባቱ ቀብር ላይ መገኘት ሲገባው፣ ይህን መሠረታዊ መብት ተነፍጎ የቀብር ስነስርዓቱ ላይ ሳይገኝ ቀርቷል። በሚያሳዝን ሁኔታም፣ ከእስር ከተፈታ ቦኃላ የአባቱን መቃብር በመጎብኘት እርሙን አውጥቶ ብዙም ሳይቆይ ራሱም በአገዛዙ ፖሊስ ለህልፈተ —ህይወት ተዳርጓል።
ወጣት ተገኝ በግፍ በተገደለበት የትላንትናው ዕለት ከጓደኞቹ ጋር በሰላም እየተጫወተ የነበረ ሲሆን፣ በፖሊስ ፓትሮል ተጭነው የመጡ የአገዛዙ ፖሊሶች “ለጥያቄ ትፈለጋለህ” በማለት ያቀረቡለትን ጥያቄ በሰላም ተቀብሎ ወደ ሽሮ ሜዳ 02 ፖሊስ ጣቢያ ከደረሰ ቦኃላ ግን፣ የአገዛዙ ፖሊስ ያለ ምንም ከልካይ በዜጎች ላይ በየዕለቱ በሚፈፅመው ፋሺስታዊ ድርጊት መሠረት፣ በደቦ በአሰቃቂ ሁኔታ ከተደበደበ ቦኃላ፣ በክላሽ ጥይት በግፍ ተገድሏል።
ይህን ፋሺስታዊ ድርጊት ተከትሎ፣ ብዙ ግፎችን ተሸክሞ የኖረው የአዲስ አበባ ህዝብ ተቃውሞውን ለማሰማት በተወሰነ ደረጃ በሽሮ ሜዳ አካባቢ ወደ አደባባይ ወጥቷል። በዚህ የተደናገጠው አገዛዙ፣ የሟችን ስም ለማጠልሸት የተለያዩ የሀሰት ትርክቶችን እየፈጠረ በመገናኛ ብዙሃን እያሰራጨ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ህዝብ ከተጋረጠበት የጄኖሳይድ አደጋ በተጨማሪ፣ በጥላቻ የታወረ እና እጅግ ዘረኛ የሆነ ኦህዴዳዊ አገዛዝ ተጭኖበት የአገዛዙን ቀንበር በልዩ ሁኔታ የተሸከመ መሆኑን መላ ኢትዮጵያዊያን እና የዓለም አቀፉ ማህበረሰቡ አፅእኖት ሊሰጡት ይገባል። አዲስ አበባ ጥቁሮች በጥቁሮች ላይ የጫኑት አፓርታዳዊ አገዛዝ የሰፈነባት ልዩ አፍሪቃዊ ከተማ ሆናለች።
በተለይ፣ የመከላካያ ሠራዊቱ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዲኒሮ እና ቶፊቅ መደድ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሻሚነት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር እና ምክትል ኮሚሽነር ሆነው ከቅርብ ግዜ በፊት ከተመደቡ ቦኃላ፣ ከተማዋም እንደ አማራ ክልል ከፖሊስ ይልቅ በወታደራዊ ጥበቃ ሰር እንድትሆን በአገዛዙ መወሰኑ በገሃድ ታይቷል። በዚህ ሁኔታ በከተማዋ ላይ የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተባባሱ እና ተቋማዊ ይዘታቸው ይበልጥ ስር እየሰደደ የሚሄድ ይሆናል።
አዲስ አበባ በርካታ የዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ከ100 በላይ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች ያሉባት እና የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ከመሆኗ አንጻር፣ ዓለም አቀፋዊ ጀረጃ ያለው የፖሊስ ኃይል የሚያስፈልጋት ከተማ ናት። ሌተናል ጄኔራል አስራት ዲኒሮ እና ቶፊቅ መደድ እንደዚህ ዓይነቱን የፖሊስ ሠራዊት ፈፅሞ ሊገነቡ የሚችሉ አይደሉም።
የአዲስ አበባ ሚዲያ ምክር ቤት በወጣት ተገኝ ባልቻ ላይ የተፈጸመውን የግፍ ተግባር በጽኑ ያወግዛል። ድርጊቱንም በአንድ ባለ ብሩህ ተስፋ ወጣት ላይ የተቃጣ ጥቃት ብቻ አድርጎ የማያየው ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ እየተፈፀመ ካለው ስርዓት ተኮር አፈና፣ ዘረፋ፣ ማፈናቀል፣ እና የጅምላ ሀብት እና ንብረት የማውደም ዘመቻ፣ እንዲሁም የጄኖሳይዱ አደጋ አካል አድርጎ ነው የሚመለከተው።
በዚህ አጋጣሚ፣ የሽሮ ሜዳ ነዋሪ ወደ አደባባይ ወጥቶ ያሰማውን የአደባባይ ተቃውሞ እንደምናደንቅ እንገልፃለን። የአዲስ አበባ ሕዝብ በራሱ ሜዳ፣ በራሱ ህዝብ፣ በራሱ አደረጃጀት፣ በራሱ አግባብ ከተከፈተበት የህልውና ጦርነት ራሱን የመከላከል ትግሉን ዳግም እንዲያቀጣጥል ጥሪም እናቀርባለን። ፍትህ ከአምባገነኖች እጅ በልመና የሚገኝ ሳይሆን፣ በመላው ሕዝባችን እጅ ያለ እና በክንዳችን ማስጠበቅ የሚገባን ሰዋዊ የተፈጥሮ መብት ነው።
የአዲስ አበባ ሚዲያ ምክር ቤት በወጣት ተገኝ ባልቻ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ፣ ፈጣሪ ነፍሱን በአፀደ ገነት እንዲያኖረው፣ ቤተሰቡን እና ወዳጆቹን እንዲያፅናናልን በአፅእኖት እንለምነዋለን።
/
የአዲስ አበባ ሚዲያ ምክር ቤት፣
ግንቦት 1፣ 2026 ዓ.ም










You must be logged in to post a comment.