
የአፋህድ ወቅታዊ መግለጫ!!!
/
በአማራ ላይ በአገዛዙ ወታደሮች የሚፈፀሙ የጾታ ጥቃቶች የጄኖሳይድ ወንጀሎች ስለሆኑ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት(UN) አፋጣኝ እርምጃ ሊወስድ ይገባል!!!
/
ህዳር 12፣ 2018 ዓ.ም።
/
በአማራ ክልል በሴቶች እና በህጻናት ላይ የአገዛዙ ጦር አባላት በሰፊው የሚፈፅሙት የጾታ ጥቃቶች ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሱ በመሄድ ላይ ናቸው። በታሪክ ጄኖሳይድ በተፈፀመባቸው ሀገራት በውል እንደታየው፣ የፆታ ጥቃት የጄኖሳይደሮች አንደኛው ተመራጭ መሣሪያ ነው። የጥቃት ሰለባዎቹ እድሜ ከ 8 ዓመት አንስቶ እስከ 70 ዎቹ ድረስ መሆኑ፣ ዓላማው ከወሲባዊ አርካታ ይልቅ ህዝብን በሥነ ልቦና ሰብሮ ለተጨማሪ እልቂት እንዲመች ማድረግ መሆኑን በተጨባጭ ያሳያል።
አማራ ከመንግሥታዊ የጅምላ ጭፍጨፋ ራሱን ለመከላከል እንደ ህዝብ ወደ ትጥቅ ትግል ከገባበት 2015 ዓ.ም አንስቶ፣ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች የተፈፀመባቸው ህፃናት እና ሴቶች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው።
እነዚህ ጥቃቶች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የተፈፀሙት በገጠራማ አካባቢዎች ወይም አንሰተኛ ከተሞች በመሆኑ፣ የህክምና ተቋማት በአቅራቢያ ስለሌሉ አብዛኞቹ ወንጀሎች ተሸፋፍነው ይገኛሉ። ሆኖም፣ አመቺ ሁኔታ ከተፈጠረ ብዙዎቹ ተሸፋፍነው እንደማይቀሩ በጉዳዩ ዙሪያ ጥናት ያደረጉ አካላት አረጋግጠዋል።
ስለዚህም፣ እንዲህ ዓይነቱ አፀያፊ ወንጀል በጅምላ ሲፈፀም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በዝምታ ፈፅሞ ሊያልፈው የሚችልበት አግባብ የሌለ በመሆኑ፣ በተባበሩት መንግሥታት (United Nations) የበላይነት ገለልተኛ የምርመራ ቡድን ተቋቁሞ የሚከተሉት እርምጃዎች እንዲወሰዱ እንጠይቃለን :-
1—በአማራ ክልል ባለው ጦርነት የተፈፀሙ የጾታ ጥቃቶችን የሚመረምር የባለሙያዎች ቡድን በተባበሩት መንግሥታት አስተባባሪነት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተውጣጥቶ እንዲቋቋም፣
2— በአማራ ክልል ያሉ ተፋላሚ ወገኖች ለመርማሪ ቡድኑ ያለ ምንም ቅድመና ሁኔታ ቅድሚያ እውቅና እንዲሰጡ፣ በሚቆጣጠሯቸው መሬቶች መርማሪ ቡድኑ በነፃነት እንዲንቀሳቀስ እንዲፈቅዱ፣ ለመርማሪ ቡድኑ የደህንነት ዋስትና እንዲሰጡና ሙሉ ትብብር እንዲያደርጉ፣
3— መርማሪ ቡድኑ በሚያወጣው የመጨረሻ ሪፖርት መሠረት ተጠያቂዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ፣
4— በተባበሩት መንግስታት አስተባባሪነት ለተጎጂዎች ደረጃውን የጠበቀ የሕክምና ክትትል ከነፃ መድኃኒት ጋር እንዲሰጥ እና የስነ-ልቦና ድጋፍ እንዲደረግላቸው እንጠይቃለን።
የጄኖሳይደሮች የተቀነባበረ ሰለባ የሆኑ የአማራ ህፃናት እና ሴቶች ድምፅ ሊሰማ ይገባል። በይበልጥም ፍትህ ሊያገኙ ይገባል። የተባበሩት መንግሥታት በአፋጣኝ እርምጃ ሊወስድ ይገባዋል። የዘገየ ፍትህ እንደ ተነፈገ ፍትህ ይቆጠራል።
ክብር እና ሞገስ ጥቃት ለደረሰባቸው የአማራ ህፃናት እና ሴቶች!!!
ድል ለአፋህድ እና የአማራ ፋኖ ሁሉ!!!
ድል ለአማራ ህዝብ!!!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
/
ህዳር 12፣ 2018 ዓ.ም።







You must be logged in to post a comment.