የኦሮሚያ ክልል ለሚያስገነባው አዲስ ቤተ-መንግስት ማሰሪያ ከወር ደመወዛችን ላይ ተቆርጦብናል ሲሉ በሶማሊያ ሰላም ማስከበር የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ቅሬታ አቀረቡ።

ሞዐ ሚዲያ – Moa Media
ሰኔ ፳፬ ፳፻፲፭ ዓ.ም
ሸዋ- ዘ ሚኒሊክ
አዲስ አበባ – ጣይቱ
በአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ስር ሆነው በሰላም ማስከበሩ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን የሰራዊት አባላት ከሚከፍላቸው ወርሃዊ ደመወዝ ላይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በአዲስ አበባ ከተማ ለሚያስገነባው ቤተ-መንግስት ማሰሪያ የሚሆን ኢትዮጵያውያን ወታደሮችን በወከሉ አመራሮች በኩል እንደተቆረጠባቸው ነው የገለፁት።
በሶማሊያ ሰላም ማስከበር የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ወታደሮችን ጨምሮ በሀገር ውስጥ የሚገኙ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት በቦረና ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ በሚል እያንዳንዳቸው ከደመወዛቸው ላይ 25% እንደተቆረጠባቸው ይታወቃል።
በዚህም ከተቆረጠብን 25% ገንዘብ ላይ በቦረና ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ብቻ ሳይሆን በአማራ ክልል የተለያዩ አከባቢዎች ላይ ተጠልለው ለሚገኙ የእለት ደራሽ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖችም ይሰጥልን የሚል ጥያቄ ያቀረቡ የሰራዊቱ አባላት ታፍነው የተሰዱ ሲሆን የደረሱበት አለመታወቁንም የአማራ ድምፅ ከወራት በፊት የአይን እማኞችን ጠቅሶ መዘገቡ አይዘነጋም።
በአሁን ሰዓት በአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ስር ሆነው በሶማሊያ ሰላም ማስከበር የተሰማሩ ከሰባት ሺ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ይገኛሉ የተባለ ሲሆን ከባለፈው ወር ጀምሮ ከወርሀዊ ደመወዛቸው ላይ እየተቆረጠባቸው መሆኑን ነው ተናግረዋል።
የሰራዊት አባላቱ፡ “ግዳጁን ስንጨርስ ከሚከፈለን ብር ተጨማሪ በየወሩ ለኪስ 38 .33 $ እና ለሻይ ቡና ተብሎ ደግሞ 6.90 $ በድምሩ 45.23 ዶላር አትሚስ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ይከፈለን ነበር ነገር ግን አሁን ላይ ለኪስ ተብሎ ከሚሰጠን ገንዘብ ላይ 22 $ ለሻይ ቡና ተብሎ ከሚሰጠን ላይ ደግሞ 4.7$ በድምሩ 26.70 $ ተቆርጦብናል” ሲሉ ገልፀዋል።
በተጨማሪም አባላቱ “በምን ምክኒያት ደመወዛችን ሊቆረጥ ቻለ በሚል ላቀረብነው ጥያቄ እስከ አሁን ይፋዊ ምላሽ ባናገኝም ነገር ግን ከውስጥ አዋቂ አመራሮቻችን ባገኘነው መረጃ መሠረት ደመወዛችን የተቆረጠው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በአዲስ አበባ ከተማ ለሚያስገነባው ቤተ መንግስት ማሰሪያ መሆኑን ደርሰንበታል” ብለዋል።
“ህይወታችንን ገብረን የሀገራችንን ክብር ለማስጠበቅ በሰው ሀገር እየተሰቃየን ባለንበት ካለችን ደመወዝ ላይ ተቆርጦ የንፁሀንን ነፍስ መታደግ ለማይችለው የኦሮሚያ ክልል መንግስት ተሰቶብናል፣ ይሄ ህገ ወጥነት ነው” ሲሉ የገለፁት በሶማሊያ ሰላም ማስከበር የተሰማሩት ኢትዮጵያውያን ወታደሮች “በቀጣይ ዋስትና ስለሌለን ተልዕኳችንን ትተን መውጣት እንጀምራለን፤ ይህንንም ከወዲሁ ህዝብ ይወቅልን” ስለማለታቸው የዘገበው አማራ ድምጽ ሚዲያ ነው።
You must be logged in to post a comment.