
ቀጣይ የሚዘጋው ቅድስት ሥላሴ ካቴዴራል
………………………………………………………….
ሞገድ እጅጉ
አብይ አህመድ ያቀዳቸው ነገሮች ሁሉ ገና ሲጀመሩ ‹‹ይሄ እንኳን አይሆንም! ይህ በፍፁም አይታሰብም! አይረግም!›› የተባሉ ናቸው፡፡ ዳሩ ግን ሁሉም ተፈጽመዋል፡፡ የአብይ አህመድን አገር አፍራሽ እቅዶች ‹‹ዓላማው ይህ ነው›› ብለው የሚናገሩ ሰዎችን ‹‹የመቃወም ሱስ!›› ሲባሉ ነበር፡፡ ዳሩ ግን አብይ አህመድ ብዙ የማይታመኑ የሚመስሉ ነገሮችን አድርጓል፤ ይፈጸማሉ ተብለው የማይታሰቡ ነገሮችን ፈጽሟል፡፡
አራት ኪሎ እና ፒያሳን ሰው አልባ ጫካ ለማድረግ የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን የመንቀል ሥራ ሊሰራ መሆኑን ትናንት ገልጸናል፡፡ ዋና ዓላማውም ሠራተኞች በአካባቢው የፈጠሩትን ማህበራዊ መስተጋብር ማፍረስ ነው፡፡ ትዝታን ማጥፋት ነው፡፡ አራት ኪሎና ፒያሳ ሙሉ በሙሉ እንዳልነበሩ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ነው አስቀድሞ ካፌዎችና በአካባቢ የነበሩ ሻይ ቤቶች ሁሉ ሳይቀር እንዲፈርሱ ያደረገው፡፡
በቀጣይ የሚዘጉት ደግሞ አራት ኪሎና ፒያሳ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ናቸው፡፡ እነዚህም አራት ኪሎ የሚገኙት ቅድስት ሥላሴ ካቴደራል ቤተ ክርስቲያን፣ አራት ኪሎና አምስት ኪሎ መሃል ላይ የምትገኘው መንበረ ፓትርያርክ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን እና ፒያሳ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳማት ናቸው፡፡ እነዚህን ገዳማት የመዝጋትና የማፍረስ ዘመቻው ከመኖሪያ ቤቶችና ከመሥሪያ ቤቶች ለየት ይላል፡፡ እንዴት የሚለውን በዝርዝር እንመልከት፡፡
የአራት ኪሎው ቅድስት ሥላሴ ብዙ ማህበራዊ ሕይወት የተገነባበት ነው፡፡ ብዙ ወጣቶች ያሉበት ነው፡፡ በብዙ ማህበራዊ ጉዳዮች ውስጥ ‹‹የአራት ኪሎ ወጣቶች፣ የሥላሴ ወጣቶች›› ይባላል፡፡ እነዚህ ወጣቶች ተወልደው ባደጉበት አራት ኪሎ አካባቢ በመሰረቱት ማህበራዊ ሕይወት የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ወዲህ ደግሞ አብዛኞቹ የኦርቶዶክስ አማኞች ስለሆኑ በቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በጽዋ ማህበር፣ በሰንበት ትምህርት ቤትና በሌሎች ቤተ ክህነታዊ ስነ ስርዓቶች የተሳሰሩ ናቸው፡፡
ነባራዊ እውነታው ይህ ከሆነ፤ የአብይ አህመድ አገዛዝ ለሚዘረጋው ወንጌላዊ ሥርዓት እነዚህን ነገሮች ማፍረስ አለበት፡፡ ወንጌላዊው የአብይ አህመድ አገዛዝ ኦርቶዶክስን ማጥፋት ተቀዳሚ ዓላማው እንደሆነ በንድፈ ሀሳብም በተግባርም ላለፉት ስድስት ዓመታት ታይቷል፡፡ የኢትዮጵያ አገራዊ ምንነት የተገነባው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳ ቤተ ክርስቲያን ጥበባዊ ሥራዎች መሆኑን ያውቃል፡፡ የኢትዮጵያ ባህል እና ማህበራዊ ሕይወት የተመሰረተው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መሆኑን ያውቃል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያን ማጥፋት የሚፈልግ አካል ተቀዳሚ ሥራው የሚሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መሰረቶችን ማጥፋት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋና ዋናዎቹ አራት ኪሎና ፒያሳ ያሉት ስለሆኑ እነዚህን አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ሰው አልባ ማድረግ አዋጪ ስልት ሆኖ አግኝቶታል፡፡
ቅድሥት ሥላሴ ካቴደራል ቤተ ክርስቲያን በአገር አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ ነው፡፡ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ እንግዶች ሁሉ የሚገበኙት ትልቅ ደብር ነው፡፡ ከአገር መሪ እስከ ታዋቂ አርቶስቶች የሚቀበሩበት ነው፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ትልቅ አገራዊ ምስል ፈጥሯል፡፡ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ምስል ፈጥሯል፡፡ ስለለዚህ አብይ አህመድ ይህን መሰረት ማፍረስ አለበት፡፡
መንበረ ፓትርያርክ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ስም እና አገራዊ ምስል ያላት ናት፡፡ ከቅድስት ማርያም ስም ከዩኒቨርሲቲ እስከ ሌሎች ተቋማት ድረስ ተሰይሞበታል፡፡ በአራት ኪሎና አምስት ኪሎ አካባቢ ያሉ የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት አድራሻቸውን ሲጠቅሱ እንደ ማጣቀሻ የሚጠቀሙት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን ነው፡፡ ተሽከርካሪዎች ቦታ የሚጠሩት በቅድስት ማርያም ነው፡፡
ስለዚህ በወንጌላዊው ብልጽግና አገር የማፍረስ ዘመቻ ተቀዳሚው ሥራ እነዚህን ምስሎች ማጥፋት ነው፡፡ ይህን ለማጥፋት ደግሞ ከዚያ አካባቢ ያሉ ተቋማትን ማፍረስ እና ታክሲዎች ወደዚያ እንዳይሄዱ በመከልከል ስሟ የሚጠራበትን አጋጣሚ መዝጋት ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ በዚያ አካባቢ ምንም አይነት ጉዳይ እንዳይኖር ማድረግ ማለት ነው፡፡
የፒያሳው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከዓድዋ ዘመቻ ዘመን ጀምሮ ላለፉት 128 ዓመታት ማህበራዊ ሕይወት ገንብቷል፡፡ ‹‹የአራዳው ጊዮርጊስ›› የሚለው ስም ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ይታወቃል፡፡ በዚህ አካባቢ ብዙ ማህበራዊ መሰረቶች ተጥለዋል፡፡ ስለዚህ ወልጌላዊ አገር ለመገንባት እነዚህ መሰረቶች መፍረስ አለባቸው ማለት ነው፡፡
እነዚህ ትልልቅ ገዳማት ይፈርሱ ዘንድ የአብይ አህመድ አገዛዝ ምን አደረገ?
አካላዊ ገጽታቸውን (ሕንጻውን) ከማፍረሱ በፊት ሰው አልባ ማድረግ ጀመረ ማለት ነው፡፡ በአካባቢው ያሉ መኖሪያ ቤቶችን አፍርሶ ነዋሪ አልባ አደረገው ማለት ነው፡፡ በአካባቢው የነበሩ ንግድ ቤቶችንና መስሪያ ቤቶችን በማፍረስ ሰው አልባ አደረገው ማለት ነው፡፡ ለሥራ እንኳን የሚሄዱ ሰዎች ቢያንስ በዓመታዊ ንግስ በዓላት ቀን ጎራ እንዳይሉ በአካባቢው ያሉ መስሪያ ቤቶችን መንቀል አዋጪ ሆኖ አገኘው ማለት ነው፡፡
በአካባቢው የነበሩ ነዋሪዎች ከሌሉ ለዓመታዊ ንግሥት በዓላት የሚደረጉ ዝግጅቶች አይኖርም፤ ድምቀቱ አይኖርም፡፡ የሰንበት ትምህርት ቤቶችና የጽዋ ማህበራት አይኖሩም፡፡ ከየካ አባዶ እና ከሰሚት ሄደው አራት ኪሎና ፒያሳ ይህን ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ በአጭሩ አካባቢው በረሃ ይሆናል ማለት ነው፡፡
አራት ኪሎና ፒያሳ እየተሰሩ ያሉ ነገሮች መናፈሻዎችና ፓርኮች ናቸው፡፡ ስለዚህ አራት ኪሎና ፒያሳ ከዚህ በኋላ ልክ እንደ ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ናቸው ማለት ነው፡፡ ሰዎች አራት ኪሎና ፒያሳ እየሄዱ ሳር እና ቅጠል ጎብኝተው የሚመለሱበት ይሆናል ማለት ነው፡፡
እንዲህ እንዲህ እያለ ከዓመታት በኋላ ምናልባትም እነዚህ ገዳማት አካላዊ ገጽታቸውም ሊፈርስ ይችላል ማለት ነው፡፡ ታሪክ ሆነው ይቀራሉ ማለት ነው፡፡ ከላይ በገለጽነው መሰረት መኖሪያ ቤቶችና መስሪያ ቤቶች ከፈረሱ ማህበራዊ ግንኙነቱ እንደሚጠፋ ምንም ማሰላሰል ያማያስፈልገው ሀቅ ነው፡፡ ማህበራዊ ግንኙነቱ ከፈረሰ እነዚህ ገዳማት ሰው አልባ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡
ፐያሳ ላይ ትልልቅ የንግድ ሴንተሮች ይሰራሉ ተብሏል፡፡ ሥራው የተሰጠው በአገዛዙ ምደባ መሰረት ራሱ ለሚፈልጋቸው ወገኖች ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ንግዱን የሚይዘው የአገዛዙ ወገን ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡ አገዛዙ የሚፈልገው ኃይል ደግሞ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ውጭ የሆነው ወንጌላዊ ኃይል እና የአገዛዙ ብሔር ወገን ነው፡፡
በአጠቃላይ፤ የአዲስ አበባ ሕዝብ ዓይኑ እያየ ቤቱን ብቻ ሳይሆን እምነቱንም ተቀምቷል!
You must be logged in to post a comment.