
‹‹ከመንግሥት ኃይል ጋር ተቃውሞ የለንም››
……………………………………………………….
ሞገድ እጅጉ
የብአዴን ተላላኪነት አስቂኝ ነው፡፡ ፕሮፖጋንዳ እንኳን መሥራት አይችልም፡፡ የሚዋሸው ውሸት ‹‹ውሸታሙን እረኛ›› ያስንቃል፡፡ ውሸታሙ እረኛ በተደጋጋሚ ‹‹አንበሳ መጣብኝ›› እያለ ይጮሃል፡፡ ሊረዱት የሄዱ ሰዎች ውሸት ሆኖ ያገኙታል፡፡ በተደጋጋሚ እየወሸ ሲያስቸግራቸው ጩኸቱን እየሰሙ ተውት፡፡ አንድ ቀን ግን የምርም አንበሳ መጣበት፡፡ ቢጮህ ቢጮህ የሚደርስለት ሰው ጠፋ፡፡ ምክንያቱም ሲዋሽ ስለኖረ አላመኑትም፡፡
የብአዴን የሰሞኑ ፕሮፖጋንዳ እንደዚያ ነው፡፡ የብአዴን ልሳን የሆነው የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ሰሞኑን ከኦህአዴግ የተሰጠውን ትዕዛዝ እያጧጧፈ ነው፡፡ የኦህዴድ ሰዎች ጥላቸውን እንኳን የማያምኑ ፈሪዎች ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት የአብይ አህመድን አረመኔያዊ አገዛዝ ለመቃወም የአማራና የትግራይ ኃይሎች አንድ ይሆናሉ የሚል ስጋት አለባቸው፡፡ ይህን ደግሞ የኦህዴድ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ አንፀባርቀዋል፡፡
ይህ ያስጨነቀው የአብይ አህመድ አገዛዝ እዚህ ግባ የማይባልና ሕጻን ልጅ እንኳን የሚንቀው አስቂኝ ፕሮፖጋንዳ አሰበ፡፡ ይሄውም፤ መነሻውን ከመቀሌ ያደረገ የጦር መሳሪያ አማራ ክልል ገብቶ ለፋኖ እየተከፋፈለ ነው የሚል ነበር፡፡ በዚህ በጣም ተሳቀበት፤ የሚቀበለው አጣ፡፡
አሁን ደግሞ የአማራን ሕዝብ በስስ ጎኑ የገባ መስሎት ‹‹ወያኔ ዳግም ወረራ ጀመረ›› የሚል ዜና የብአዴን ልሳን በሆነው አሚኮ በተከታታይ ማሰራጨት ጀምሯል፡፡
ክርክሩ ወያኔ ጥቃት አይፈጽምም አይደለም፡፡ የተዘገበበት መንገድ በጣም የሚያስነቃ እና ራሳቸውን ትዝብት ላይ የሚጥል መሆኑ ነው፡፡ የምርም ወያኔ ጥቃት ቢከፍት እንኳን የሚነሳ ሰው እንዳይኖር የሚያደርግ የእረኛው አይነት ውሸት መሆኑ ነው፡፡ የዜናው መልዕክት የአብይ አህመድን አገዛዝ የምትቃወሙ ፋኖዎች አርፋችሁ ተቀመጡ የሚል ነው፡፡ የብአዴን ልሳን የሆነው አሚኮ የሰራው ዜና ላይ ይህ ዜና ቃል በቃል ሰፍሮ ይገኛል፡፡
‹‹በራያ አላማጣ ወያኔን ለመቃወም የወጡ ሰልፈኞች ‹ከመንግሥት ኃይል ጋር ተቃውሞ የለንም› አሉ›› ይላል፡፡ እነዚህ ሰልፈኞች እነ ማን ናቸው? በአብይ አህመድ አገዛዝ ከሕጻን እስከ አዛውንት በድሮን የሚጨፈጨፍ አማራ እንዴት ይህንን ሊል ይችላል? በፍፁም የአማራ ሕዝብ ይህንን ሊል አይችልም፡፡
ይህን ማለት ያስፈለገበት ምክንያት የአብይ አህመድ ሠራዊት የፋኖን ክንድ መቋቋም ሲያቅተው ሕዝቡ ከአብይ አገዛዝ በኩል ነው ለማስባል ነው፡፡ በቀበሌ አስገድዶ ባወጣቸው ሰልፈኞች የራያ ሕዝብ አስመስሎ ለማጭበርበር ነው፡፡ ሰልፈኞቹ የወጡት ወያኔን ለመቃወም ቢሆን ኖሮ ይህኛው ፕሮፖጋንዳ ለምን አስፈለገ? ‹‹ከመንግሥት ኃይል ጋር ተቃውሞ የለንም›› ማለት ለምን አስፈለገ?
እንዲህ አይነት የሕጻን አስተሳሰብ ራሱን ነው የሚጎዳው፡፡ ታማኝነት ያሳጣዋል፡፡ ዜናውን የተጠቀመው ለአማራ መሬት ብሎ ሳይሆን ሥልጣኑን ለማዳን ብቻ ብሎ እንደሆነ በግልጽ አሳወቀ፡፡
የአብይ አህመድ አገዛዝ የአማራ ሕዝብ ‹‹ወያኔ›› ሲባል ምንም ሳያስብና ሳያሰላስል ግርርር ብሎ ይወጣል የሚል እምነት አለው፡፡ ካለፈው ስህተቱ አይማርም የሚል ንቀት አለው፡፡ ስለዚህ ይቺን ፕሮፖጋንዳ ይጠቀማል፡፡ ወያኔ ጥቃት ባይከፍት እንኳን ወያኔ የከፈተው አስመስሎ ራሱ ጥቃት ይከፍታል፡፡ ምክንያቱም ሥልጣኑን ለማዳን የትኛውንም አይነት ሴራ ይጠቀማል፡፡ ሥልጣኑን ለማዳን ደግሞ የአማራን ሕዝብ ይከፋፍላል ያለውን ዘዴ ሁሉ ይጠቀማል፡፡
የብአዴን ልሳን ሰሞኑን እነዚህን ዜናዎች በተደጋጋሚ እየሰራ ነው፡፡ ከሥር የሚሰጡት የአንባቢዎችና የአድማጭ ተመልካቾች ግብረ መልስ ግን የተነቃበት መሆኑን እና የተላላኪው ብአዴን ተላላኪነት መሆኑን የሚገልጽ ነው፡፡ ዳግም የሚሸወድ እንደማይኖር የሚገልጽ ነው፡፡ ዋናው ጠላት ብአዴንና የአብይ አህመድ አገዛዞች መሆናቸውን የሚገልጽ ነው፡፡
የአብይ አህመድ አገዛዝ ይህን ፕሮፖጋንዳ የፈለገው ለአማራ ሕዝብ አስቦ ነው የሚል አማራ ካለ እጅግ በጣም የዋህ ነው ማለት ነው፡፡ ሲደረጉ የነበሩ ሴራዎች ሁሉ አልገቡትም ማለት ነው፡፡ ከትናንት ስህተቱ አልተማረም ማለት ነው፡፡ ዛሬም ራቅ አድርጎ ማሰብ አልቻለም ማለት ነው፡፡
ጉዳዩ፤ ወያኔ አያደርገውም አይደለም! ዳሩ ግን በአብይ አህመድ አገዛዝ ትዕዛዝ እና በብአዴን አስፈፃሚነት የሚደረግ ነገር ሁሉ ለአማራ የማይሆን መሆኑን ማወቅ ነው፡፡ መቼም የብአዴን ልሳን የሆነው አሚኮ ከአብይ አህመድ አገዛዝ ዕውቅና ውጭ በራሱ ውሳኔ ነው ያደረገው ማለት ከየዋህነትም ያለፈ የጤና ችግር ጭምር ነው፡፡ በብአዴን የሚመራ ተቋም በምንም አይነት ሁኔታ በራሱ ውሳኔ ምንም ነገር አያደርግም፡፡ ይህንን ላለፉት 33 ዓመታት አይተናል፡፡
በዚህ ሎጂክ መሰረት ከሄድን፤ ይህ አጀንዳ ያለአንዳች ምክንያት እንዲሰራጭ አልተደረገም፡፡ ይህን ሸፋፋ የሆነ ሴራ መረዳት የማይችል አይኖርም፡፡
ይቺን ጥያቄ ደጋግመን እናስብ! ‹‹ከመንግሥት ኃይል ጋር ተቃውሞ የለንም›› የሚለው ለምን አስፈለገ?
You must be logged in to post a comment.