በሟች የሚቀናው የአብይ መንግስት

በሟች የሚቀናው የአብይ አህመድ አገዛዝ
…………………………………………………..
ሞገድ እጅጉ
የየካቲት 12 ሰማዕታት ሀውልት የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በወራሪው የጣሊያን ፋሽስት የተጨፈጨፉ ኢትዮጵያውያን ሰማዕታትን ለማሰብ የተሰራ ሀውልት ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከዜሮ ለመጀመር የተነሳው የአብይ አህመድ አገዛዝ ደግሞ ከ2010 ዓ.ም በፊት የነበሩ የኢትዮጵያ ምልክቶችን ሁሉ የማጥፋት ዘመቻ ላይ ነው፡፡ ከዚያ በፊት በነበሩት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ሁነቶች ውስጥ የለሁበትም ብሎ ያምናል፡፡ በዚህም ምክንያት እንደ ዓድዋ ያሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደነቁ ድሎችን ሁሉ ሳይቀር የማጥፋት ዘመቻ ላይ እንደነበር አይተናል፡፡ የምኒልክን አደባባይ ስሙ እንዳይጠራ ‹‹ዓድዋ 00›› ብሎ ሰየመው፡፡ ሀውልቱ እንዳይታይ ከአጠገቡ የካድሬ መሰብሰቢያ የሚሆን አዳራሽ ሰርቶ ስሙንም ግብሩንም አጠፋው፡፡
አሁን ደግሞ በሞቱት እንኳን ቀንቶ እነሆ የየካቲት 12 ሰማዕታት መታሰቢያ ሀውልት እንዳይታይ ከፊት ለፊቱ ይህን ትልቅ ሕንጻ አስገንብቷል፡፡ ያስገነባው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስም ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው እንዲህ አይነት ሕንጻ የለውም፡፡ የተሰራው ለዚሁ ዓላማ ይመስላል፡፡
ብዙ ሰዎች ነገሩን ቀለል አድርገው ‹‹ይሄ እንኳን የመቃወም ሱስ ነው›› ማለታቸው አይቀርም፡፡ ዳሩ ግን ባለፈው ሳምንት የኪነ ሕንጻ ባለሙያዎች አስተያየት ሲሰጡበት እንደነበረው፤ ከአንድ ትልቅ ታሪካዊ ሀውልት አጠገብ እሱን የሚበልጥ ሌላ ነገር መሥራት አይቻልም፡፡ እንዲያውም ባለማስተዋል እና በግዴለሽነት ነው የሰሩት እንዳይባል እንኳን የኪነ ሕንጻና የታሪካዊ ቦታዎች ህግ ይከለክላል፡፡ ይህን ያደረገው ደግሞ የአንዲት አገር ችግሮች ይጠኑበታል በሚባለው በአገሪቱ ከፍተኛው የትምህርት ተቋም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ የኪነ ሕንጻ፣ የታሪክ እና የቅርስ ትምህርት በሚሰጥበት ከፍተኛው የትምህርት ተቋም ነው፡፡
አንድን ታሪካዊ ቦታ የሚከልል ነገር ሲሰራ መንግሥት ያስፈርሳል፡፡ ስለዚህ ዩኒቨርሲቲው በግለደለሽነት ሰርቶት እንኳን ቢሆን አገሪቱ መንግሥት ቢኖራት ኖሮ ያስፈርሰው ነበር፡፡ ዳሩ ግን ኢትዮጵያን ከዜሮ የመጀመር ዘመቻ ላይ ያለው አገዛዝ በራሱ ፍላጎትና ውሳኔ ለማሰራቱ ስሙና ግብሩ ገላጭ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ስሪት ውስጥ ድርሻ የለኝም ብሎ የሚያስበው የአብይ አህመድ አገዛዝ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር፣ ክብርና ነፃነት ለማስጠበቅ መስዋዕት በሆኑ ጀግኖች ይቀናል፡፡ የእነዚያ ጀግኖች አርበኞች ስም ሲነሳ የአሁኑ የኢትዮጵያ መደፈር እንዳይነሳ ይፈልጋል፡፡ የቀድሞዎቹ ጀግኖች አርበኞች ታሪክ ሲነሳ ‹‹ምነው ግን አሁን ምን ነካል?›› በሚል ይህ ተውልድ መቆጨት እንዳይኖረው ይፈልጋል፡፡ ለዚህም እንደ መፍትሔ የወሰደው ቀደም የነበረችዋን ኢትዮጵያ የሚያስተውሱ ነገሮችን ሁሉ ማፍረስና ማጥፋት ነው፡፡ ለዚህም እንደ አበባው አያሌው ያሉ ሆዳም የታሪክ ባለሙያ የሚባሉ ካድሬዎችን እያማከረ ታሪክ እንዴት መጥፋት እንዳለበት መሥራት ነው፡፡
በአብይ አህመድ አገዛዝ ውስጥ የአበባው አያሌው ድርሻ ታሪክና ቅርስ እንዴት እንደሚጠፋ ማማከር ነው፡፡ ታሪክ እንዴት እንደሚጠበቅ በተማረው ትምህርት እንዴት መጥፋት እንዳለበት ስለሚያውቅ እንዲህ አያነት ዘዴዎችን ይነግረዋል፡፡ ለዚህም ነው ከአንድ ታሪካዊ ሀውልት አጠገብ ሀውልቱን የሚጋርድ ነገር መኖር የለበትም የሚለውን ወስዶ የሚጋርድ እንዲሰራ ያማከረው፡፡
የካቲት 12 የሰማዕታት ሀውልት ከዚህ በኋላ ልክ እንደ ጀግኖቹ ሰማዕት ሆኗል ማለለት ይቻላል፡፡ ከዚህ በፊት ከርቀት ይታይ የነበረው ሀውልት አሁን እንዳይታይ ተደርጓል፡፡ ከዚህ በፊት እንደ ምልክት ይጠቀስ የነበረው ሀውልት አሁን እሱን የሚበልጥ ሌላ ምልክት እንዲኖር ተደርጓል፡፡ ከርቀት ፎቶ ሲነሳ ከካሜራ ይገባ የነበረው ሀውልት አሁን ከጀርባው ያለው ሕንጻ እንዲሸፍነው ተደርጎ ተሰርቷል፡፡
አሁን የሰማዕታት ሀውልት እንኳን በሌላ አቅጣጫ ከዩኒቨርሲቲው ሕንጻ በተቃራኒ አቅጣጫ ሆኖ እንኳን ሀውልቱ አይታይም፡፡ ይህ በምሥሉ ላይ የምታዩት ፎቶ የተነሳው ከሀውለቱ አጠገብ ሆኖ ነው፡፡ ለዚያውም ከዩኒቨርሲቲው ሕንጻ በተቃራኒ ሆኖ ነው፡፡ ከስድስት ኪሎ አካባቢ ሆኖ ሀውልቱ ጭራሹንም ከነመኖሩም አይታይም ማለት ነው፡፡
የአብይ አህመድ አገዛዝ ይህን የሚያደርገው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ምልክት ናቸው የሚባሉ ነገሮችን ሁሉ ማይፋት ስላለበት ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከዜሮ ሲጀምር ከዚህ በፊት የነበሩ ነገሮች እንዳይታዩ ወይም እንዲጠፉ በማድረግ ነው፡፡
ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ምልክቶች ሁሉ በአብይ አህመድ አገዛዝ እንዲጠፋ ወይም እንዲደበዝዝ ያልተደረገ እስኪ ምን አለ?

Discover more from wenchifEthiopia.com ወንጭፍ ኢትዮጵያ

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading